የኢድ አል ፈጥር በዓል ዛሬ በድምቀት ተከበረ!

የኢድ አል ፈጥር በዓል ዛሬ በድምቀት ተከበረ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– 1ሺህ 442ኛው የኢድ አል ፈጥር በዓል፣ ዛሬ ባህርዳር፣ አዳማ፣ ጎንደር፣ መቱ፣ ኮምቦልቻ፣ አሰላ፣ ጂንካ፣ ጭሮ፣ በጋምቤላ ክልል፣ በጅማ፣ በአፋር ክልል፣ በደሴ፣ በሐረሪ ክልል፣ ሃዋሳ፣ ደብረታቦር፣ ሻሸመኔና ሌሎች ከተሞች፣ በሶላት ስግደት ስነ ስርዓት ተከብሯል፡፡

በዓሉ በተለይም፣ በአዲስ አበባ ስታዲየም የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት በድምቀት የተከበረ ሲሆን፣ በክብር እንግድነት የተገኙት የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክትል ከንቲባዋ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ባደረጉት ንግግር “በብሔርና በሐይማኖት ሊነጣጥሉን የሚፈልጉ ሀይሎች ማወቅ ያለባቸው፣ ኢትዮጵያ ትንሽ ሲገፏት የምትወድቅ የእንቧይ ካብ አለመሆኗን ሊገነዘቡ ይገባል” ብለዋል።

“የአብሮነት እሴቶቻችን እና የውስጥ አንድነታችን በማጠናከር ከሁሉም አቅጣጫ የሚደረግብንን ጫና መከላከል አለብን” ያሉት ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ “በረመዳን ጾም የተከናወኑ መልካም ተግባራት በቀጣይነት ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ዒድሪስ በበኩላቸው “ሕዝበ ሙስሊሙ ከኢትዮጵያውያን እህት ወንድሞች ጋር አንድነቱን በማጠናከር ጠላቶቹን በጋራ መመከት ያስፈልጋል” ሲሉ ገልጸዋል።

“አንድ ከሆንን ወደ ሰላም ከተመለስንና ከተደማመጥን የውጭ ኃይሎችን በመመከት ግድቡን ከዳር እናደርሰዋለን” በማለትም ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ዒድሪስ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፣ ዛሬ “ቢላሉል ሐበሺ ሙዚየም”ን መጎብኘታቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት “ዛሬ የዒድ አልፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ የቢላሉል ሐበሽን ማዕከል ጎብኝቻለሁ። ማዕከሉ የኢትዮጵያውያንን ችግሮች ለመፍታት፣ ድኾችን ለመርዳትና ዕውቀትን ለማስፋፋት የሚያደርገው ጥረት አስደናቂ ነው። በተለይም የረዥም ዘመናት ታሪክ ያለውን የኢትዮጵያን እስልምና ቅርሶች ለማሰባሰብና ለትውልዱ ለማሳየት የመሠረተው ሙዝየም በከተማችን ሊጎበኙ ከሚገባቸው ቦታዎች አንዱ ነው። ተቋሙ ከዚህ የበለጠ ነገር ለኢትዮጵያ እንደሚሠራ እምነቴ ነው” ብለዋል።

LEAVE A REPLY