አይበገሬው ጄነራል ኃይሌ መለስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ!

አይበገሬው ጄነራል ኃይሌ መለስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜናሥመ ጥሩውና አይበገሬው ጄኔራል ኃይሌ መለስ፣ ለረዥም ጊዜ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ባለፈው ማክሰኞ ግንቦት 2 ቀን 2013 ዓ.ም በተወለዱ በ80 ዓመታቸው በባሕርዳር ከተማ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

ጄኔራል ኃይሌ መለስ በስደት ይኖሩበት በነበረው ኒውዚላንድ አገር፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት ስትሮክ መቷቸው በጸና ታመው፣ ሕመሙ ባስከተለው መዘዝም የመርሳት ችግርና ሌሎችም እንደ መናገር አለመቻል ዓይነት በሽታዎች ገጥመዋቸው የአልጋ ቁራኛ ሆነው ጥቂት ዓመታትን አሳልፈዋል። ሕመማቸው እየበረታባቸው ሲሄድም፣ ልጃቸው ወደሚኖርበት አውስትራልያ በመሄድ አገር ቤት እስከገቡበት ጊዜ ድረስ ቆይታቸውን እዚያው አድርገዋል።

ከዚያም በቤተሰብ ውሳኔና በራሳቸውም የቆየ ኑዛዜ “ስሞት ወያኔ ከሥልጣን የሚወርድ ከሆነ፣ ለሀገሬ አፈር እንድታበቁኝ” ባሉት መሠረት ሕመማቸው እየባሰ መሄዱ ሲታወቅ፣ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ተደርጎ ከ6 ወራት ቆይታ በኋላ በተወለዱ በ80 ዓመታቸው ሕይወታቸው አልፏል።

ስለ ሥርዓተ ቀብራቸው ከቤተሰብ አካባቢ በተገኘው መረጃ መሠረት፣ ዛሬ ቅዳሜ በባሕርዳር ከተማ በሚገኘው ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን ከጧቱ 3 ሶስት እስከ 6 ሰዓት ባለው ጊዜ ጸሎተ ፍትሐት ተደርጎላቸዋል። ከዚያም አስከሬናቸው በቤተሰብ፣ ዘመድ አዝማድና በአካባቢው ኗሪዎች እንዲሁም በወታደራዊ ማርሽ ታጅቦ ወደ ትውልድ ከተማቸው ደብረ ታቦር በክብር ተሸኝቷል። ነገ ዕሁድ ግንቦት 8 ቀን 2013 በአጅባር ሜዳ ጸሎተ ፍትሐት ተደርጎም በደብረታቦር መድኃኔዓለም ቤተክርስትያን ሥርዓተ ቀብራቸው ይፈፀማል።

የጀነራሉ አስከሬን ዛሬ በባሕር ዳር ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ሥርዓተ ፍትሃት ተፈጽሞለት በተሸኘበት ወቅት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ፣ የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ አብረሃምን ጨምሮ የሃይማኖት አባቶች፣ የትግል ጓደኞቻቸው፣ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው የተገኙ ሲሆን፣ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድሩ ዶ/ር ፈንታ ማንደፍሮ “ጄኔራል ኃይሌ ኢትዮጵያ በተፈተነችበት ቀን የፈተናዋን ጥያቄ የመለሱ ታላቅ ጀግና ነበሩ፡፡ ያረፉበት ዘመንም ኢትዮጵያ መልሳ በተፈተነችበት ጊዜ በመሆኑ ለዚህ ትውልድ ታላቅ መልዕክት አለው፡፡ በዚያድባሬ የተመራው የሶማሊያ ጦር ኢትዮጵያን ሲወር፣ ጦር እየመሩ ሀገር ነጻ ያደረጉ ጀግና ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን እንደ ቅርጫ ስጋ ሊካፈሏት የፈለጉ ሁሉ ባሰፈሰፉበት ጊዜ በአጭር ቀን አሰልጥነው መቁሰልን እሾህ እንደመውጋት ሳይቆጥሩ ነጻ የሚያወጡ ልጆች ዛሬ አለን ወይ?… ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ ታፍሰው ሳይሆን መርጠው ወታደር የሆኑ፣ ያዋጉ፣ ኢትዮጵያ አምጣ የወለደቻቸው የጦር ጠበብት ናቸው። ለኢትዮጵያ ሕዝብ የአንድት ቀንዲልም ናቸው። ኢትዮጵያ በተወረረችበት ኹሉ የዘመቱ ነጻ ያወጡ፣ ድንበራቸው ኢትዮጵያ የሆነች ናቸው። ጄነራሉ የጦር መሪ ብቻ ሳይሆኑ ፖለቲከኛና የአስተዳደር ሰውም ነበሩ” ብለዋል።

“ብርጋዴል ጄኔራል ኃይሌ የነጻነት፣ የአንድነት፣ የጀግንነት ፊደል ስለሆኑ ፊደል ይነበባል እንጂ አይሞትም፤ ይነበባሉ ይቀጥላሉ፤ ልጆቻችንም የእርሳቸውን ጀግንነት ይማሩታል” ሲሉም ዶክተር ፈንታ በጄኔራሉ አስከሬን ሽኝት ላይ ተናግረዋል።

ጄኔራል ኃይሌ መለስ ማን ናቸው?

ጀግናው፣ ቆራጡና የሀገር ፍቅር ስሜት ከህሊናቸው ሳይደብዝዝ ሕይወታቸው ያለፈው ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ መለስ ተሰማ፣ በድሮው አስተዳደራዊ አወቃቀር በደብረታቦር አውራጃ፤ በፋርጣ ክምር ድንጋይ ምክትል ወረዳ፣ መገንዲ ጊዮርጊስ ደብር፣ ጋይድባ በተባለች ደብር፣ ሥመ-ጥር እና አንደበተ ርቱዕ ከነበሩት አባታቸው ፊታውራሪ መለስ ከተማ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ዘውዲቱ ተሰማ ጥር 28 ቀን 1933 ዓ. ም ተወለዱ።

ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም መምሕር ተቀጥሮላቸው በመንፈሳዊ ትምህርት ዳዊት ለመድገም በቅተዋል። ከዚያም ወደ ዘመናዊ ት/ቤት በማምራት የ6ኛ ክፍል ትምህርታቸውን አጠናቀዋል። ወላጅ አባታቸውን ገና በልጅነታቸው በሞት በመነጠቃቸው የቤተሰቡ ኃላፊነት በእርሳቸው ትከሻ ላይ ወደቀ። በዚህም ምክንያት መደበኛ ትምህርታቸውንም ለማቋረጥ እንዲገደዱ አብቅቷቸዋል።

ገና በጠዋቱ መደበኛ ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ቢገደዱምና የቤተሰብ ኃላፊነት አደራ ተሸካሚ ለመሆን ቢበቁም፣ ወደ ጄኔራልነት ማዕረግ እስከ ማሻቀብ ያደረሳቸውን የውትድርና ሙያ የሚያስቀጥል ክስተት በ1960 ዓ.ም ገጠማቸው። በተጠቀሰው ዓመትም የኢትዮጵያ መንግሥት የብሔራዊ ጦር ሻለቆች ውስጥ አንዱ በሆነው 11ኛ ሻለቃ ወረታ ላይ በተቋቋመው ተቋም ገብተው በመሠረታዊ የእግረኛ ጦር ትምህርት ቤት ገብተው ለመሰልጠን በቅተዋል።

በዚሁ ሥልጠና ከእርሳቸው በጣም የተሻለ የቀለም ትምህርትና ወታደራዊ ልምድ የነበራቸውን በመብለጥ አንደኛ በመውጣታቸው የጦሩን ክፍል ማስደመም ችለዋል። በወቅቱ ሠልጣኞችን ለመመረቅ የመጡት ቀዳማዊ ዓፄ ኃይለ ሥላሴ የብሔራዊ ጦር ኮርሰኛ አንደኛ መውጣቱን ሲሰሙ ማመን አቅቷቸው “በቃ! ጦር ሠራዊቱ ሞቷል ማለት ነው” በሚል መንፈስ ቅር ይላቸዋል በማለት፣ ጄኔራል ኃይሌ በ2ኛ ደረጃ እንደወጣ ተደርጎ፣ የካቲት 23 ቀን 1963 ዓ.ም ከንጉሠ ነገሥቱ እጅ ልዩ የብዕር ሽልማት እንዲያገኙ ተደርጓል።

ጄኔራል ኃይሌ መለስ ካከናወኗቸው ተግባራት ጥቂቶቹ፤

– ከየካቲት 1963 እስከ 1965 ዓ.ም፣ በደብረዘይት ሻለቃ ብሔራዊ ጦር ውስጥ የትምህርት መኮንን ሆነው ለሁለት ዓመታት አገልግለዋል።

– በፊቼ ስላሌ እና በመናገሻ አውራጃ 2ኛ ሻለቃ ብሔራዊ ጦር ለ6 ወራት በትምህርት መኮንንነት ሠርተዋል።

– ከሀምሌ 7 ቀን 1965 ዓ.ም እስከ ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ በነበረው የብሔራዊ ጦር ጠቅላይ መምሪያ የትምህርት መኮንን በመሆን ለአንድ ዓመት አገልግለዋል።

– ከሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ. ም ጀምሮ ከደርግ አባላት አንዱ በመሆን በተለያዩ የሥራ ክፍሎች የመሩ ሲሆን ከነዚህም
ሀ/ የደርግ አስተዳደርና መከላከያ ኮሚቴ አባል፣
ለ/ የጎንደር ክፍለ ሀገር የደርግ የቡድን መሪና በተግባር ተመድበው ባይሰሩበትም የጎንደር ክፍለ ሀገር ቋሚ የደርግ ተጠሪ ሆነው አገልግለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በንግድና ቱሪዝም ሚ/ር ቋሚ የደርግ አባል፣
ሐ/ በሐረርጌ ክፍለ ሀገር የደርግ ጽ/ቤት የፓለቲካና የሕዝብ አደረጃጀት አስተባባሪ በመሆን ለ 3 ወራት ያህል አገልግለዋል።

– የሶማሌ ጦርነት ተዋጊ እና አዋጊ መኮንን
ከ 1969-1970 ዓ.ም ከወራሪው ሶማሌ ጋር በተደረገው ጦርነት ጄኔራል ኃይሌ የ69ኛው ሚሊሻ ብርጌዱን በማሰልጠንና በግንባር አዋጊ ሆነው በመምራት ታላቅ ጀብዱ የሰሩ ምርጥ መኮንን ናቸው።

በመስከረም ወር 1970 ላይ በድሬዳዋ ግንባር ወደ ውጊያው የገቡት ጄኔራል ኃይሌ፤ ካራማራን፣ ጅጅጋን፣ ደገሐቡርንና መጨረሻም ላይ መጋቢት 1 ቀን 1970 ዓ.ም ቀብሪደሐርን ከሶማሊያ ወራሪ ጦር ነፃ አውጥቶ በመቆጣጠር፣ የምሥራቁ ግንባር ጦርነት በድል እንዲጠናቀቅ ያደረገውን ብርጌድ የመሩ እኒሁ ሥመ ጥሩው ጄኔራል ኃይሌ መለስ ነበሩ። የካራማራ ገድል ሲነሳ ሥማቸው ከሚጠሩት ባለታሪክ ጀግኖች መካከል ጄኔራሉ አንደኛውና ግንባር ቀደሙም ናቸው።

– ገና በሻለቅነት ማዕረግ እያሉ የባሕርዳር አውራጃ አስተዳዳሪ፣ ከነሐሴ 1970 ዓ.ም ጀምሮ ለ5 ዓመታት ያህል የባሕርዳር አውራጃ አስተዳዳሪ በመሆን አስተዳደራዊ ጥበብ በተሞላበት ስልት በከተማው ውስጥ የነበሩ ምሁራንን እና ኗሪውን ሕዝብ ከጎናቸው በማሰለፍና በቅንነት በማስተባበር አመርቂ ሥራ እንደሰሩ ዛሬም ምስክርነቱን የሚሰጧቸው ቁጥራቸው ቀላል አይደለም።

– ከሚያዝያ 1975 እስከ ግንቦት 1980 የሸዋ ክፍለሀገር ወታደራዊ ኮሚሳር፣ ግንቦት ወር 1980 እስከ 1981 ዓ.ም የትግራይ ክፍለ ሀገር ራስ ገዝ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ፣ ከጥር 19 ቀን 1981 ዓ.ም እስከ የካቲት 1983 የደቡብ ጎንደር ክፍለ ሀገር ኢሠፓ 1ኛ ፀሐፊ በመሆን አገራቸውን አገልግለዋል።

የደርግ መንግሥት ሽንፈት ሲገጥመውም “እጅ የመስጠትን ታሪክ አልወረስኩም፣ የምንታወቅበት ባሕላችንም አይደለም” በማለት ለበርካታ ዓመታት በአገር ውስጥ በልዩ ልዩ ሥፍራዎች ዱር-ቤቴ ብለው እየተዘዋወሩ ሲታገሉ ከቆዩ በኋላ ከእርሳቸው አልፎ ዘመድ አዝማዶቻቸው ጭምር ጄኔራል ኃይሌን አምጡ እየተባሉ መሳደዱ ስለበዛባቸው ወደ ጎረቤት አገር መሰደድ ግድ ሆነባቸው።

በመጀመሪያ ወደ ኬንያ ከዚያም ወደ ሱዳን በማምራት የሚቻላቸውን ሁሉ አደረጉ። ወያኔ ከሱዳን መንግሥት ጋርም በመመሳጠር ለእስር እስከ መዳረግ አብቅቷቸዋል። አገራቸውንም አጥተው፣ በጎረቤት አገርም መሳደዱና እስሩ ሲበዛባቸው የሱዳን መንግሥትም አሳልፎ ሊሰጣቸው መዘጋጀቱ ስለተደረሰበት በስተመጨረሻ ርቀው ወደ ኒውዝላንድ ሊሰደዱ ግድ ሆነባቸው። የሚወዷት አገራቸው በሕይወት ሊኖሩባት ባይታደሉባትም በሕይወታቸው ፍፃሜ አፅማቸው አርፎባታል።

ጄኔራል ኃይሌ መለስ፣ በሕይወት ዘመናቸው ለሚወዷት አገራቸው በሰጧት ቅን የህይወት አግልግሎት፣
– የሕብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ታላቅ የክብር ኮከብ ኒሻን፣
-የየካቲት 66 አብዮት ኒሻን 1ኛ ደረጃ
– አውስትራሊያ ፐርዝ ኗሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን እ.ኤ.አ የካቲት 22 ቀን 2020 የላቀ አርበኝነትና ወታደራዊ አገልግሎት ዕውቅና አንጸባራቂ ታሪካቸውን ከመዘክራቸውም በላይ የሜዳሊያና የዋንጫ ሽልማት አበርክተውላቸዋል።

ጄኔራል ኃይሌ፣ ቁጡ የሚሆኑትና ደማቸውም የሚፈላው በኢትዮጵያ ጠላቶች ላይ እንጂ፣ እንደ ሰው ግን በጣም ደግ፣ ርህሩህ ትህትናን የተላበሱ፣ ትንሽ ትልቁን አክባሪ ሰው እንደነበሩ የሚያውቋቸው ሁሉ ይመሰክሩላቸዋል።

ጄኔራል ኃይሌ መለስ ባለትዳር፣ የ7 ልጆች እና የ13 የልጅ – ልጆች አያት ለመሆን የበቁ ሰው ነበሩ።

LEAVE A REPLY