ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የብዝኃ ሳተላይት መረጃ መቀበያና መቆጣጠሪያ ጣቢያ በእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪና ምርምር ማዕከል፣ የሠመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የመርካቶ ዘመናዊ የከተማ አውቶብስ ተርሚናል እና የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ያስገነባቸው አራት የአየር መቆጣጠሪያ ታወሮች ዛሬ በልዩ ልዩ ስነ ስርዓት ተመርቀዋል።
በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ግንባታው የተከናወነው የብዝኃ ሳተላይት መረጃ መቀበያና መቆጣጠሪያ ጣቢያው ሙሉ በሙሉ በመንግሥት
ወጪ በተደረገ ሦስት ሚሊዮን ዩሮ የተገነባና ሁለት ዓመት የፈጀ መሆኑ ሲታወቅ፣ የሳተላይት መረጃ ፍላጎትን በአይነት፣ በጥራትና በመጠን በማሟላት መረጃው ለተለያዩ የልማት ተግባራት እንዲውል የሚያስችለው ጣቢያው 7 ነጥብ 3 ሜትር ከፍታ እንዳለው፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ ተቋማት ለሳተላይት መረጃ የሚያወጡትን የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስቀር ተገልጿል፡፡
በተያያዘ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከጅቡቲ ቆይታቸው ሲመለሱ፣ በ50 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈውንና 5 ሺህ 500 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው ስምንት የማምረቻ ህንፃዎችን የያዘውን የሠመራ ኢንዱስትሪ ፓርክን ዛሬ የመረቁ ሲሆን፣ ፓርኩ ሀገሪቱ እየተገለገለችበት ከምትገኘው የጁቡቲ ወደብ እና ሌሎች በአቅራቢያ ለሚገኙ ወደቦች በቅርብ ርቀት ላይ መገኘቱ፣ በወጪ ንግድ ዘርፍ ለሚሰማሩ አምራቾች ሳቢ ያደርገዋል ተብሏል።
በተመሳሳይ፣ የመርካቶ ዘመናዊ የከተማ አውቶብስ ተርሚናል፣ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበት
ዛሬ ተመርቆ ተከፍቷል።
ተርሚናሉ በ200 ሚሊዮን ብር የተገነባና በ4 ሺህ 125 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን፣ በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ምክትል ከንቲባዋም
“የመርካቶ የአውቶቢስ ተርሚናል በመርካቶና አካባቢው ያለውን ከፍተኛ የህዝብ እንቅስቃሴ የትራንስፖርት እጥረት መቅረፍና ምቾትን ይጨምራል” ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ኢ/ር ስጦታው አከለ በበኩላቸው፣ ይህ የከተማ አውቶቡስ ተርሚናል በመርካቶ አካባቢ የሚስተዋለውን የትራንስፖርት መጨናነቅ ለመቀነስ በአንድ ሰዓት 6 ሺህ፣ በቀን ደግሞ እስከ 80 ሺህ የትራንስፖርት ተጠቃሚዎችን ማስተናገድ እንደሚያስችል ገልፀዋል።
እንደዚሁም፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ አድርጎ ያስገነባቸው አራት የአየር መቆጣጠሪያ ታወሮች ዛሬ መመረቃቸው የታወቀ ሲሆን፣ ታወሮቹ የተገነቡት በኦሮሚያ ክልል ባሌ ሮቤ ከተማ፣ በአማራ ክልል ኮምቦልቻ፣ በሲዳማ ክልል ሀዋሳ እና በሶማሌ ክልል ጎዴ ከተማ መሆኑን ከባለስልጣኑ ማህበራዊ የትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡