ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳዮች ከፍተኛ ተወካይ ጆሲፕ ቦሬል እና በህብረቱ የቀውሶች አያያዝ ኮሚሽነር ያኒዝ ሌናርቺች፣ በትግራይ ክልል የሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽነት ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
“በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ረድኤት ተደራሽነትን ወታደራዊ ኃይሎች እያያደናቀፉ መሆኑን ተመድ አረጋግጧል። የአውሮፓ ህብረት ለሁሉም አካባቢዎች የረድዔት ተደራሽነት እንዲረጋገጥ እንዲሁም የኤርትራ ወታደሮች በአስቸኳይ ከአካባቢው እንዲወጡ በተደጋጋሚ ሲጠይቅ ቆይቷል” ብለዋል።
“የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ሁለቱንም ጥያቄዎች ተፈፃሚ ለማድረግ ቃል የገቡ ቢሆንም መሬቱ ላይ የሚታየው እውነታ ግን ሰብዓዊ ቀውሱ ከሁሉም በላይ የከፋ በሆነባቸው ገጠራማ አካባቢዎች እርዳታ እንዳደርስ ወታደራዊ ኃይሎች እየከለከሉ መሆኑ ነው” ያሉት የአውሮፓ ህብረት ባለሥልጣናቱ፣ ሰብዓዊ ረድዔትን በጦርነት መሳሪያነት መጠቀም ከባድ የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ረድዔት ህግጋት ጥሰት መሆኑንና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ህይወት አደጋ ላይ የሚጥል እንደሆነ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል፣ ኢሰመኮ ከተመድ የሰብዓዊ መብቶች ተቋም ጋር በመሆን፣ በትግራይ ተፈጽመዋል የተባሉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማጣራት የተገለፀ ሲሆን፣ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፣ በጉዳዩ ላይ በሰጡት መግለጫ፣ ከሁለቱ ወገን ከእያንዳንዳቸው 6 የመርማሪ አባላትን ያካተተ የባለሙያዎች ቡድን በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ወደተመረጡ የትግራይ ክልል አካባቢዎች እንደሚያመራ ገልጸዋል።
ሁለቱ ተቋማት በትግራይ ተፈጽሟል የተባለውን የመብት ጥሰት በጋራ ለማጣራት መጋቢት ወር አጋማሽ
ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የጠቀሱት ዶ/ር ዳንኤል፣ ስምምነቱ ከተደረገ ጀምሮ የመርማሪ ቡድኑ አባላት ለምርመራ የሚያስፈልጉ የቅድመ መረጃ ማሰባሰብ፣ የቦታ ልየታ፣ የምርመራ ሥልቶችን መለየትና የትራንስፖርት ሁኔታዎች ላይ ሲመክሩ መቆየታቸውን አስረድተዋል።
የምርመራውን ነፃነትና ገለልተኝነት ለማረጋገጥ ሲባል የመርማሪ ቡድኑ አባላት የሚሄዱበትን ቦታና አካባቢ ከመጥቀስ ቢቆጠቡም፣ እንዳስፈላጊነቱ ምርመራው በሱዳን የተጠለሉ ኢትዮጵያዊያንንም ሊያካትት እንደሚችልና ምርመራውን ለማከናወን ሦስት ወራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።