ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና የወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ በኩል መደበኛ ፓስፖርት ለማውጣት ከወራት በላይ የሚፈጅ መሆኑ በተገልጋዮች ዘንድ ቅሬታ ያስነሳ ሲሆን፣ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙጂብ ጀማልም ቅሬታው ተገቢ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የፓስፖርት ቀጠሮ የተራዘመው ኤጀንሲው በርካታ ተግዳሮቶች ያሉበት በመሆኑ እንደሆነ የገለፁት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር “የኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና የወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ከዚህ ቀደም ይፋ እንዳደረገው መደበኛ ፓስፖርት ለማግኘት ከ75 ቀናት ወደ 30 ቀናት ማውረዱን ቢናገርም በአሁኑ ወቅት መደበኛውን ፓስፖርት ለማግኘት ወራቶች እየወሰደ ያለው የተገልጋዩ ቁጥር በመጨመሩ ምክንያት ነው” ብለዋል።
ከዘንድሮ ጥቅምት ወር ጀምሮ ለተጠቃሚዎች በድረ-ገጽ አማካይነት አዲስ ፓስፖርት ለማውጣትና ለማደስ ቀጠሮ ማስያዝ የሚያስችል ስርዓት ይፋ አድርጎ ሲሰራ መቆየቱን ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙጂብ “ይህን ተከትሎ ኤጀንሲው በቀን ውስጥ በአካል ያስተናግድ ከነበረው ከ800 እስከ 1000 የሚደርስ የደንበኞች ቁጥር ወደ 4000 እና 5000 እንዲያድግ አድርጎታል፤ በዚህም በወር እስከ መቶ ሺ ደንበኞችን እንድናስተናግድ ተገደናል” ሲሉ ተናግረዋል።
አክለው “ማንኛውም ግለሰብ ባለበት ቦታና ሁኔታ በቀላሉ በኦንላይን ለመመዝገብ መቻሉ የአገልግሎት ፈላጊውን ቁጥር ከፍ አድርጎታል። ይህን ከፍተኛ ቁጥር ደግሞ ኤጀንሲው ባሉት ውስን መስሪያ ቤቶች፣ የአገልግሎት መተግበሪያ እቃዎችና የሰው ሀይል አቅም ለማስተናገድ አለመቻሉ የቀጠሮው ጊዜ እንዲራዘም ምክንያት መሆኑን ያመለከቱት ዋና ዳይሬክተሩ “ተቋሙ ያለበትን ውስንነት በመቅረፍ መስራት እንዳለበት የሚታወቅ ቢሆንም አሁን ላይ ተገልጋዮች በትዕግስት በመጠበቅ በቀጠሯቸው ቀን መገልገል ይችላሉ” ብለዋል።