ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ነገ አርብ ግንቦት 13 ቀን 2013 ዓ.ም፣ በአዲስ አበባ በሚገኙ የተመረጡ ኤምባሲዎች ደጃፍ፣ ከጠዋቱ 4:00 ሰአት ጀምሮ የታቃውሞ ሰልፎች የሚካሄዱ ሲሆን፣ የሰልፎቹ አላማም “ብሔራዊ ክብር፣ በህብር’ በሚል ዋነኛ መልዕክት ስር፣ ምዕራባዊያንን ‘እጃችሁን አንሱ’ ለማለት” መሆኑ ተገልጿል።
የሰልፎቹ አደራጆች ትናንት በራዲሰን ብሉ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “በኢትዮጵያ ከለውጡ ወዲህ እየተባባሰ እና እየጨመረ የመጣ የውጭ ጣልቃ ገብነት እና ተጽዕኖ ይታያል። በተለይም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ የህግ ማስከበር ዘመቻ እና የዜጎች መብት የሆነውን የምርጫ ስርዓት በመታከክ በልዩ ልዩ መንገዶች ጣልቃ የሚገቡ አገራት እና ተቋማት እየተበራከቱ ሉዓላዊነታችንንም እየተዳፈሩ ስለሆነ እነዚህ ጸረ ኢትዮጵያ አቋም ያላቸው አገራትና አለም አቀፍ ተቋማት ከኢትዮጵያ እጃቸውን እንዲያነሱ እንጠይቃለን” ብለዋል።
“እነዚህ አገራት እና ተቋማት በሚሰጧቸው መግለጫዎችና በሚያወጧቸው ዘገባዎች ኢትዮጵያውያንን መናቅ፣ ታሪካቸውን መዘንጋት፣ የዜጎች ድህነት ለሀገር ያላቸውን ፍቅር እንዳጠፋባቸው አይነት ድምዳሜ ይታይባቸዋል። ለዚህም ኢትዮጵያን አስመልክቶ የሚያወጧቸውን መግለጫዎች፣ ዛቻዎችና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች መመልከት በቂ ነው። ሆኖም እኛ በምንም ጉዳይ የማንሰበር በመሆናችን እጃችሁን አንሱልን ልንል ተዘጋጅተናል” ሲሉ በዚሁ መግለጫቸው የገለፁት የሰልፎቹ አስተባባሪዎች “ምዕራባዊያኑም ሆኑ አሜሪካዊያን እኛን ለመገሰጽና ስለ ዴሞክራሲ ለመስበክ የሞራል ልዕልና የላቸውም” ብለዋል።
‘ብሄራዊ ክብር፣ በህብር’ በተሰኘው የነገው የተቃውሞ ሰልፍ ከኢትዮጵያ በተቃራኒ በቆሙት ላይ ተቃውሞ የማሰማትና ኢትዮጵያን ያከበሩትን ደግሞ የማመስገን ዕቅድ መያዙን የገለፁት የሰልፎቹ አዘጋጆች፣ ነገ አርብ ከረፋዱ 4:00 ሰዓት ጀምሮ በሚካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ “ኢትዮጵያዊነትን ለመሸርሸር እየሰሩ ይገኛሉ” ለተባሉት አሜሪካ ኤምባሲ፣ እንግሊዝ ኤምባሲ፣ ግብጽ ኤምባሲ፣ ሱዳን ኤምባሲና ለአውሮፓ ህብረት በተወካዮች አማካኝነት የተቃውሞ ደብዳቤዎች እና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሰበሰቡ ፊርማዎች የሚገቡ ሲሆን፣ ከቀኑ 10:00 እስከ 11:00 ሰዓት ባለው ጊዜም ኢትዮጵያዊያን “በአንድነታችንና በሉዓላዊነታችን ላይ የሚመጡብንን ማናቸውንም ሀይሎች አንታገስም” በሚል በያሉበት ድምጻቸውን የሚያሰሙበት እና በአንጻሩም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንን ደግፈው “ከጎናችን የቆሙ” ለተባሉት የቻይና፣ የራሽያ እና አፍሪካ ህብረት የምስጋና መልእክቶች እንደሚተላለፉ አመልክተዋል።
“ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህንን ጥሪ በመቀበል በታቃውሞ እና በድጋፍ ድምጽ ማሰማቱ ላይ የኮቪድ ፕሮቶኮል ጠብቆ እንዲሳተፍ” ሲሉም አዘጋጆቹ ጥሪ አቅርበዋል።