ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በጉለሌ ክ/ከተማ ወረዳ 7፣ 61 ሰዎችን ጭኖ ወደ ባህር ዳር ይጓዝ የነበረ ‘ታታ’ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ከቅጥቅጥ አይሱዙ ጋር፣ ዛሬ ጠዋት 1:30 ሰዓት ላይ ተጋጭቶ በደረሰ የትራፊክ አደጋ፣ 46 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አስታውቋል፡፡
በትራፊክ አደጋው ሁለቱም መኪናዎች ተገልብጠው 46 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት ከመድረሱ በስተቀር እስካሁን ምንም የሞተ ሰው አለመኖሩን የገለፁት በአዲስ አበበ ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያ ኃላፊ የሆኑት ዋና ኢንስፔክተር ማርቆስ ታደሰ፣ በትራፊክ አደጋው የተጎዱ ሰዎች ወደ አቤት ሆስፒታልና ሌሎች የህክምና ማዕከላት መወሰዳቸውን፣ የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መሆኑንና የተገለበጡ መኪናዎች በክሬን ተነስተው መንገዱ ለትራፊክ ክፍት መደረጉን ጠቁመዋል።
“የሱሉልታ መንገድ ዳገታማ፣ ጠመዝማዛማና ቁልቁለታማ በመሆኑና ስፍራው ከዚህ በፊትም በተለያዩ ጊዜያት በርካታ አደጋዎች ሲያስተናግድ የነበረ አካባቢ እንደመሆኑ አሸከርካሪዎች ይህን ተረድተው ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸዋል” ሲሉም ኢንስፔክተር ማርቆስ አሳስበዋል።