ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ኢትዮጵያ በቀጣይ ወራት ልታከናውን ያቀደችው የታላቁ ህዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት፣ በግብጾች የውኃ አቅርቦት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደማይኖረው የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሹክሪ ተናግረዋል።
ለዜጎቻቸው በአስዋን ግድብ ውስጥ በቂ የውኃ ክምችት መኖሩንና ኢትዮጵያ የምታካሂደው ሁለተኛ የግድቡ ውኃ ሙሌት ሀገራቸውን በአሉታዊ መልኩ ሊጎዳ እንደማይችል የገለፁት ሳሚ ሹክሪ፣ ጥንቃቄ የተሞላበት የውኃ አያያዝ በመጠቀም ይህን ማለፍ እንደሚቻልም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በመጪው የክረምት ዝናብ ወቅት ሁለተኛውን የግድቡን ሙሌት ለማካሄድ መዘጋጀቷን አጽንኦት ሰጥታ በይፋ መግለጽ በጀመረችበት በዚህ ወቅት የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይህን መናገራቸው፣ የተጀመረው መጠነ ሰፊ የዲፕሎማሲ ጥረት ውጤት ነው ተብሎለታል።
የህዳሴው ግድብ አጠቃላይ ግንባታ ሂደት ከ80 በመቶ በላይ መድረሱን የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር መግለጹን በርካታ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ከትናንት ጀምሮ እየዘገቡት መሆኑንም ለመረዳት ተችሏል።