ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሶሊያና ሽመልስ በምርጫው ሂደት ዙሪያ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፣ ግንቦት 28 ቀን ሊካሄድ የነበረው ሀገራዊ ምርጫ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም እንዲካሄድ በቦርዱ መወሰኑን አስታውቀዋል።
የምርጫ ሂደቱ በኹሉም የመራጮች ምዝገባ በተጠናቀቀባቸው ቦታዎች ብቻ እንደሚካሄድ የገለፁት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሯ “ከመራጮች ምዝገባ ጋር አቤቱታ የተነሳባቸው እና ምዝገባውን ዘግይተው የጀመሩ እና ያላጠናቀቁ የምርጫ ክልሎች እና ጣቢያዎች ላይ ግን በዚሁ ቀን አይካሄድም” ብለዋል።
ምዝገባው ከተቀመጠለት ቀን ዘግይቶ የመካሄዱ ምክንያት፣ ምርጫ ቦርድ ማከናወን ያለበትን ሥራ ለማጠናቀቅ፣ ሎጅስቲክስ እና ቁሳቁስን በማዳረስ ምርጫው በአንድ ቀን ማካሄድ እንዲችል ለማድረግ አስፈላጊ እና ተጨማሪ የምርጫ አስፈፃሚ ቁጥር ለመጨመር በማሰብ መሆኑን ዳይሬክተሯ አመለክተዋል።
እስካሁን ከ138 ሺህ 350 በላይ አስፈፃሚዎችን በማንሳት ከ106 ሺህ 345 በላይ የሰው ኃይል ለማካተት በመሥራት ላይ መሆኑን፣ ከዚህ ባለፈም የምርጫ አስፈፃሚዎች ከምርጫ እና ከውጤት ቆጠራ እንዲሁም ውጤትን ይፋ ከማድረግ ጋር ተያይዞ ስልጠና እንዲወስዱ ለማስቻል በማሰብ መራዘሙንም የምርጫ ቦርድ ሕዝብ ግነኙነት በመግለጫቸው አንስተዋል።