ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማስፈጸም 130 ሺህ በላይ አስፈጻሚዎችን መልምሎ የመራጮችን ምዝገባ እንዳጠናቀቀ መግለፁ የሚታወቅ ሲሆን፣ ሰኔ 14 ቀን 2013 ለሚካሄደው የድምጽ መስጫ ቀንም ተጨማሪ የምርጫ አስፈጻሚዎችን መመልመል እንደሚፈልግ አስታውቋል።
ቦርዱ ይህንኑ በማስመልከት ባሰራጨው መግለጫ እንዳመለከተው፣ በምርጫ አስፈፃሚነት ለመመዝገብ የሚፈልጋቸው ተከታዮቹን መስፈርቶች የሚያሟሉ ብቻ ናቸው። በዚህም መሰረት፤
– ምንም አይነት የፓርቲ አባልነት፣ የዝቅተኛ የአስተዳደር እርከኖች ላይ ሰርተው የማያውቁ፣
– ከሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ውጪ በሌሎች የቀድሞ ምርጫ የማስፈጸም ተግባራት ላይ ተሳትፈው የማያውቁ፣
– የመጀመሪያ ዲግሪ ወይም ተመጣጣኝ ረጅም አመት የስራ ልምድ ያላቸው እና በአጭር ጊዜ ኮንትራንት ለመስራት ፍቃደኛ የሆኑ በቦርዱ ድረገጽ እና ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚገኘውን ፎርም በመጠቀም በሚቀጥሉት አራት ቀናት እስከ ግንቦት 17 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ብቻ ማመልከት ይችላሉ ተብሏል።