ጎሳንና ቋንቋን ማዕከል አድርጎ በትህነግ የተዘረጋው የመንግስት የአስተዳደር መዋቅር ሳይስተካከል የሚደረግ ምርጫ ፤ ለህብረ-ብሄር ድርጅቶች እንቅስቃሴ አመቺ ባለመሆኑ የምርጫው ውድድር ፍትሃዊ አይደለም።
በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ተቀባይነት ያላት ብርቱካን ሚደቅሳ የምትመራው ምርጫ ቦርድ የምርጫውን ሂደት (ዕለታዊ ክንውኑን) ተአማኒ ሊያደርግ ቢችል እንኳ ውድድሩን ፍትሃዊ ማድረግ አይችልም።
የምርጫው ዕለት ሂደት(ድምጽ አሰጣጡ) እንከን የለሽ ከሆነ የምርጫው ሂደት ተአማኒ ነው ሊባል ይችላል ። የውድድሩ ፍትሃዊነት የሚለካው ግን የሃገሪቷ የፖለቲካ ምህዳርና የመንግስት አስተዳደራዊ መዋቅር ሁሉንም ተወዳዳሪ ድርጅቶች በእኩል አይን ባየበትና ባሳተናገደበት መጠን ሊሆን ግድ ይላል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳርና የመንግስት መዋቅር ደግሞ ተወዳዳሪ ድርጅቶችን ሁሉ በእኩል አይን በማየት አይታማም።
የፖለቲካ ምህዳራችን ለጎሳ ድርጅቶች አባት ለህብረ ብሄር ድርጅቶች እንጀራ አባት በመሆኑ ምርጫው ተዓማኒ ሊሆን ቢችል እንኳ ውድድሩ ግን ፍትሃዊ አለመሆኑን ከወዲሁ መመስከር ይቻላል።
ስለ ኢትዮጵያ ምርጫ ሳስብ ፦ በመረብ ኳስ ክለብና በእግር ኳስ ክለብ መካከል በመረብ ኳስ ሜዳ ላይ የሚደረግ የመረብ ኳስ ውድድር አይነት ኢ-ፍትሃዊነቱ ይጎላብኛል። አንዱ በሚያውቀው ሜዳና በሚያውቀው ስፖርት እንዲወዳደር ሲመቻችለት ፤ ሌላው ደግሞ በማያውቀው ሜዳና በማያውቀው ስፖርት እንዲወዳደር ተፈረደበት።
የህብረ – ብሄር ድርጅቶች እጣ ፈንታ በማያውቁት ሜዳና በማያውቁት የስፖርት አይነት እንዲወዳደሩ የተፈረደባቸው የእግር ኳስ ክለብ እጣ ፈንታ ነው ። መረብ ኳሱም ክለብ የነማን ተምሳሌ እንደሆነ አይጠፋችሁም።
ገዢው ፓርቲ ደግሞ ሁለቱንም ባህሪያት አዳቅሎ ይዟል፦ እንደ ህብረ-ብሄር “የኢትዮጵያ ብልጽግና” ነኝ እያለ፤ እንደ ጎሳ ደግሞ የኦሮሞ ብልጽግና፤ የአማራ ብልጽግና፤ የሱማሌ ብልጽግና … በሚል በሁለት ማሊያ ሊጫወት ተሰልፏል።
ይህ ማለት ደግሞ ብልጽግና ኳሷን በእጅም በእግር የመምታት ፈቃድ አለው ማለት ነው። … ከዚህ በላይ ታዲያ ምን ኢ-ፍትሃዊ ውድድር ሊኖር ይችላል?።
ውድድሩ ፍትሃዊ ሊሆን የሚችለው ሜዳውም የስፖርቱም አይነት አንድ ሲሆን ብቻ ነው።
በመጨረሻም፦ ቀጣዩ ምርጫ ፍትሃዊ ሆነም አልሆነም ለአቅመ ምርጫ የደረሰ ዜጋ ሁሉ የምርጫ ካርድ ማውጣት አለበ። ምክንያት፦ ካርድ ባለማውጣት የሚገኝ ምንም ፋይዳ አይገኝምና ነው። ምርጫው ፍትሃዊ አለመሆኑን ለማጋለጥም ቢሆን በምርጫው መሳተፍ ግድ ነው። ይህ ማንም አሌ የማይለው እውነት ይመስለኛል።
ይልቅ መነሳት ያለበት፦ የጎሳ ድርጅቶች ከጎሳቸው ውጭ ለማን አማራጭ ሊሆኑ ይችላሉ? ህብረ-ብሄር ድርጅቶችስ በጎሳ ድርጅቶቹ ባለስልጣናት ለተጠፈነገ የክልል ህዝብ እንዴት አማራጭ ሊሆኑ ይችላሉ? የሚለው ጥያቄ ነው ……
የጠበበውን አስፍተህ –
ያከረረውን አላልተህ
ሃገራችንን ሰላም አድርግልን …
አሜን!!!