ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ፣ የልማት ስራዎች እየጎበኙ በነበሩ የወረዳው አመራሮች ላይ ታጣቂዎች ባደረሱት የደፈጣ ጥቃት፣ የወረዳው ጸጥታ እና አስተደደር ጽህፈት ቤት ሃላፊን ጨምሮ 7 ሰዎች መገደላቸውና ሌሎች 5 ሰዎች ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገለፀ።
ጥቃቱን የፈፀሙት፣ በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀው ‘የሸኔ ታጣቂዎች’ መሆናቸውን የገለፁት የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ኦብሳ ሁንዴሳ “የአሸባሪው ሸኔ ታጣቂዎች ግድያውን የፈጸሙት ትናንት አመሻሽ 11:00 ሰዓት አካባቢ በወረዳው ሾሮ ጫልቤሳ ቀበሌ ነው” ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ዲላ ሪፈራል ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ያመለከቱት ኮማንደር ኦብሳ፣ ጥቃት ያደረሱ አሸባሪዎችን የማደኑ ስራ በጸጥታ አካላት በቅንጅት እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልፀው፣ የጥፋት ቡድኑን ከወረዳው ነጻ ለማድረግ የተጀመረው ዘመቻ እንዲሳካ ህብረተሰቡ ለመንግስት ያለውን ድጋፍና ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።