ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በመቀናጀት ባደረጉት ክትትል በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 በተለምዶ ላምበረት ተብሎ በሚጠራው መናኸሪያ ግቢ ውስጥ ክትትል ሲደረግባቸው እና ከአዲስ አበባ ለመውጣት ሲዘጋጁ የነበሩ ሁለት ግለሰቦች ግንቦት 10/2013 ዓ/ም ከጠዋቱ 3 ሠዓት ገደማ በያዙት ሻንጣ ላይ በተደረገ ብርበራ በላስቲክ ተጠቅልሎ የተቀመጠ 205 ሺህ 512 የአሜሪካ ዶላር፣ የተለያዩ የባንክ ሰነዶች እና ፓስፖርት ከነ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ዛሬ አስታውቋል፡፡
በተመሳሳይ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በጥናት ላይ ተመስርቶ ባከናወነው ተግባር በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ኦሎምፒያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ግንቦት 11 ቀን 2013 ዓ/ም በግምት 9 ሰዓት ገደማ በተመሳሳይ ለህገ ወጥ ዝውውር የተዘጋጀ 23 ሺህ 300 የአሜሪካ ዶላር፣ 85 ሺህ 600 የኢትዮጵያ ብር እንዲሁም 17 የተለያዩ የኤ.ቲ.ኤም ካርዶች እና 29 የተለያዩ የባንክ የሂሳብ ደብተሮች ከ4 ተጠርጣሪዎች ጋር ሊያዙ መቻሉንና በአጠቃላይ በተያዙት 6 ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ እየተጣራ መሆኑን ገልጿል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በኮንትሮባንድ የገቡ ከ 2 ሺህ በላይ ሞባይል ስልኮችን በተሽከርካሪ ሲጭን የነበረ ግለሰብ እጅ ከፍንጅ ተይዞ ምርመራ እየተጣራበት መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።
ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር የዋለው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው መርካቶ አዲስ አበባ የገበያ ማዕከል አካባቢ መሆኑን የገለፀው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ግለሰቡ በአዲስ አበባ የገበያ ማዕከል የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ቆሞ በነበረ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-A 84156 አ.አ በሆነ ተሽከርካሪ በኮንትሮባንድ የገቡ 2 ሺህ 70 የተለያዩ ሞባይል ስልኮችን እና ቻርጀሮችን በማዳበሪያ ከረጢት ሲጭን በስራ ላይ በነበሩ የክፍለ ከተማው የፖሊስ አባላት እጅ ከፍንጅ ተይዞ ተገቢው ምርመራ እየተጣራበት መሆኑን አመልክቷል።