ዛሬ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ሲጀመር ምዕመናን ሰልፍ ወጡ!

ዛሬ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ሲጀመር ምዕመናን ሰልፍ ወጡ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜናየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርሰቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ዛሬ ግንቦት 17 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰዓት በመንበረ ፓትሪያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በሚያካሂደው የጸሎት ሥነሥርዓት የተጀመረ ሲሆን “እኛ ከቅዱስ ፓትሪያርኩ ጎን እንቆማለን! የቤተ ክርስቲያን ስደት ይቁም! የምንሞትለት ሐይማኖት እንጂ የምንሞትለት ብሔር የለንም! ርካሽ ፖለቲከኞች ከቅድስት ቤተ ክርስቲያንና ከቅዱስ ፓትሪያርኩ ላይ እጃችሁን አንሱ” የሚሉና ሌሎች መፈክሮችን የያዙ ምዕመናንም ሰልፍ መውጣታቸው ታውቋል።

በመንበረ ፓትሪያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ቅዱስ ሲኖዶስ ፅ/ቤት አካባቢ መፈክር የያዙ ምዕመናን ሰልፍ ከመውጣታቸው ጋር ተያይዞ የተወሰነ ግርግር የተፈጠረ ሲሆን፣ አድማ በታኝ የፌደራል ፖሊስ በአካባቢው በብዛት ሰፍሮ የሚገኝ ቢሆንም ወደግጭት የሚያመራ አዝማሚያ ሳይፈጠር ሰልፈኞቹ ተቃውሟቸውን አሰምተው በዝማሬ ወደየመጡበት መመለሳቸውን ዘጋቢያችን በስፍራው ተገኝቶ አረጋግጧል።

ነገሮች በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ፣ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ ብጹዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና የሀገረ ስብከት ሠራተኞች በተገኙበት እስከ ቅርብ ሰዓት ድረስ በርካታ ከየአድባራቱ እና ገዳማቱ የመጡ ወጣቶች በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በተወካዮቻቸው አማካኝነት ጥያቄዎቻቸው እያቀረቡ መሆናቸውንም ለማወቅ ተችሏል።

ዛሬ በተጀመረው ጉባኤ፣ ቋሚ ሲኖዶሱ በምልአተ ጉባኤው መታየት ይገባቸዋል በማለት ያዘጋጃቸውን አጀንዳዎች ምልአተ ጉባኤው በሚሰይማቸው ብጹአን አባቶች እንዲታዩ ካደረገ በኋላ መካተት ያለባቸውን አጀንዳዎች ለይቶ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በማቅረብ የሚያጸድቅ መሆኑ ተገልጿል።

በጉባኤው የጸደቁትን አጀንዳዎች መሰረት በማድረግና በቅደም ተከተል በመወያየት ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖም የጉባኤውን መከፈት በማስመልከት የመክፈቻ መልዕክት እንደሚያስተላልፉም የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት አመልክቷል።

LEAVE A REPLY