የአፍሪካ ቀንን አስመልከተው የሩሲያው ፑቲንን ጨምሮ መሪዎች መልዕክት አስተላልፈዋል!

የአፍሪካ ቀንን አስመልከተው የሩሲያው ፑቲንን ጨምሮ መሪዎች መልዕክት አስተላልፈዋል!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና“ጥበብ ባህል እና ቅርስ የምንፈልጋትን አፍሪካ ለመገንባት ማንሻዎቻችን ናቸው” በሚል፣ የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣ የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት የተመሰረተበት ቀን ዛሬ እየተከበረ ይገኛል፡፡

ዕለቱን በማስመልከት መግለጫ ያወጣው የአፍሪካ ህብረት፣ ይህ የምስረታ በዓል በፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስኮች በአፍሪካ የተገኙ ስኬቶችን ለማጉላት እንደሚጠቅም አስታውቋል፡፡

የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት ምስረታ ቀንን ለማስታወስ በሚከበረው በዚህ የአፍሪካ ቀን የተለያዩ ሀገራት መሪዎች “የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት፣ ከቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ጋር የአሁኑ የአፍሪካ ሕብረት ውልደት 20 ዓመታትን እንዳስቆጠረ አስታውሰው “ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለነገ የተሻለ ሰላም፣ አንድነት እና ብልጽግና የጋራ ቁርጠኝነት ያስፈልገናል” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የአፍሪካ ቀንን በማስመልከት መልዕክት ያስተላለፉት
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም “የበለጸገች ሀገር ለመገንባት የሚደረገው ጉዞ በራሱ ፈታኝ ነው። ነገር ግን፣ በታላቁ አበበ ቢቂላ በተግባር እንዳየነው፣ ምቹ የሚባለው መንገድ እንኳ ባዶ እግርን ያቆስላል። የጉዞውን ስኬታማነት ራዕይን አጥርቶ በማየት እና በ“ባዶ እግር”ም ቢሆን ጎዳናውን ሳይለቅቁ በመገስገስ ይወሰናል” ብለዋል።

የአፍሪካ ቀንን በማስመልከት ለአፍሪካ ሀገራት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው፣ የአፍሪካ አገሮች በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስኮች አስደናቂ ስኬት ማስመዝገባቸውንና ወሳኝ ዓለም አቀፍ አጀንዳዎች ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ የጎላ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ገልጸው “የአፍሪካ ቀን አፍሪካውያን ቅኝ ገዥዎችን ድል ያደረጉበት፣ ለነጻነት፣ ለሰላም እና ለብልጽግና ያላቸው ተስፋ ምልክት ነው” ብለዋል፡፡

ሩስያ ከአህጉሪቱ ሀገራት ጋር ያላትን የጠበቀ ግንኙነትን በተመለከተ ከፍ ያለ ዋጋ እንዳላት የገለጹት ፑቲን፣ በአፍሪካ ሕብረት እና ቀጣናዊ ትብብሮችን በማሳደግ፣ ሁለገብ ትብብርን በማጎልበት እንዲሁም የጋራ የተጠቃሚነትን እና ቅንጅትን መፍጠር ጠቃሚነቱን አንስተው “በዚህም አካባቢያዊ ግጭቶችን ለመፍታት፣ ሽብርተኝነትን፣ አክራሪነትን፣ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን እና ወረርሽኝን ለመቋቋም እንዲሁም ሌሎች ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ የጸጥታ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያደርጉትን ጥረት በጽኑ ትደግፋለች” ሲሉ አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ፣ የአፍሪካ ህብረት ሲመሰረት የጋራ ዓላማ ይዞ በአንድነትና በትብብር መንፈስ በመመስረቱ በአንድነትና በትብብር የተሻለች አፍሪካን መፍጠር እንደሚቻል የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ባስተላፉት መልዕክት ገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ ቀንን በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት የላኩት ሚኒስትሩ፣ ቱርክ ከአፍሪካ አገራት ጋር የጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ስትራቴጂ እንደምትከተልና ሀገራቸው ለአፍሪካ አጀንዳ 2063 መሳካት ድጋፍ እንደምታደርግ አመልክተዋል።

LEAVE A REPLY