በዛሬው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ ውሎ 7 ሊቃነ ጳጳሳት አጀንዳ ቀርፀው እንዲያቀርቡ...

በዛሬው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ ውሎ 7 ሊቃነ ጳጳሳት አጀንዳ ቀርፀው እንዲያቀርቡ ተመረጡ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜናትናንት ማምሻውን የተጀመረው ዓመታዊው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ ዛሬም የቀጠለ ሲሆን፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የጉባኤውን መከፈት አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት “የሁሉም ነገር መሰረትና የችግሮች ሁሉ መፍትሔ ሰላም ብቻ ነው” ብለዋል።

“መንግስትም ሆነ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ አስፈላጊው ነገር ሁሉ ማድረግ ይጠበቅበታል” ያሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ
“ዋስትና ያለው ሰላም በሀገሪቱ ሊረጋገጥ የሚችለው፣ ሀሉም ባለ ድርሻ አካላት በጠረጴዛ ዙሪያ ተሰብስበው መወያየት፣ መግባባትና ሀገራዊ ስምምነት መድረስ ሲችሉ ነው” በማለትም በመልዕክት ገልፀዋል።

በዚሁ መልዕክታቸው ማጠቃለያም “በሀገሪቷ በተለያዩ አካባቢዎች በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ጉባኤው በጸሎት፣ በማስታረቅ፣ በቁሳቁስና በመጠለያ እንዲሁም በምግብና መጠጥ ድጋፍ ከጎናቸው ሊቆም ይገባል” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በቅዱስ ሲኖዶሱ ዓመታዊ ምልዓተ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርሰቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን ጨምሮ ሁሉም የአህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት በመሳተፍ ላይ ሲሆኑ፣
ጉባኤው ዛሬ ጠዋት የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን የመክፈቻ መልእክት ካዳመጠ በኋላ፤ ብጹዕ አቡነ ኤልያስ፣ ብጹዕ አቡነ ማቴዎስ፣ ፣ብጹዕ አቡነ ማርቆስ፣ ብጹዕ አቡነ አብርሃምን፣ ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ፣ ብጹዕ አቡነ ፊልጶስ እና ብጹዕ አቡነ ሩፋኤል አጀንዳ ቀርጸው እንዲያቀርቡ መመደቡን ለማወቅ ተችሏል።

ጉባዔው በቀጣይ ቀናት በሚኖረው ቆይታ፣ የተመረጡት ብጹአን አባቶች አዘጋጅተው የሚያቀርቧቸውን አጀንዳዎች አንድ በአንድ መርምሮና ተወያይቶ ያጸድቃቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርሰቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በመንበረ ፓትሪያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በሚያካሂደው የጸሎት ሥነሥርዓት የተጀመረ መሆኑንና “እኛ ከቅዱስ ፓትሪያርኩ ጎን እንቆማለን! የቤተ ክርስቲያን ስደት ይቁም! የምንሞትለት ሐይማኖት እንጂ የምንሞትለት ብሔር የለንም! ርካሽ ፖለቲከኞች ከቅድስት ቤተ ክርስቲያንና ከቅዱስ ፓትሪያርኩ ላይ እጃችሁን አንሱ” የሚሉና ሌሎች መፈክሮችን የያዙ ምዕመናንም ሰልፍ መውጣታቸውን ትናንት መዘገባችን ይታወሳል።

LEAVE A REPLY