አሜሪካዊው ሴናተር ማዕቀቡን ተቃወሙ!

አሜሪካዊው ሴናተር ማዕቀቡን ተቃወሙ!

የብሔራዊ ክብር ግብረ ኃይል ለእንግሊዝ ኤምባሲ መልዕክት ማድረሱን አስታወቀ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ታዋቂው የሪፐብሊካን ፓርቲ አባል እና የኦክላሆማ ግዛት ሴናተር ጂም ኢንሆፍ፣ በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሚመራው የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ኢትዮጵያ ላይ የጣለውን ማዕቀብ እንደሚቃወሙ አስታውቀዋል።

“የባይደን አስተዳደርን ጠንካራ የቪዛ እገዳ እቃወማለሁ” ሲሉ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ላይ ያስታወቁት የሴኔቱ የጦር አገልግሎት ኮሚቴ አባል ሴናተር ጂም “ግጭቶችን ለማስወገድ እየሠራች ያለችው ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የእኛ ርዳታ ነው። እንዲህ ያለ ድርጊት ወደ ሰላማዊ መፍትሄ ለመጠጋት አይበጀንም” ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ደጋግሞ እየሰጠ ባለው መግለጫ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባቷን “ተገቢ ያልሆነ እና ፈጽሞም ተቀባይነት የሌለው” ማለቱና አገሪቱ ጣልቃ ገብነቷን በዚህ መልኩ ከቀጠለችም ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጤን እንደምትገደድ ማስታወቁ ይታወሳል።

በተያያዘ፣ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚደረገውን ጣልቃ ገብነት በመቃወም “የብሔራዊ ክብር በኅብር” ግብረ ኃይል፣ ለእንግሊዝ ኤምባሲ መልዕክት ማድረሱን ያስታወቀ ሲሆን፣ ለእንግሊዝ ኤምባሲ ባደረሰው መልዕክት፣ ኢትዮጵያ እየገነባች ያለችውን የታላቁ ህዳሴ ግድብን አስፈላጊነት ገልፆ፣ የሀገሪቱን የምርጫ ፍላጎት እና ሉዓላዊነት እንዲያከብሩና በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ መጠየቁንም አመልክቷል።

ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ኢትዮጵያ የምታደርገውን ጥረት መደገፍ እንደሚገባ በመልዕክቱ ያሳሰበው ግብረ ኃይሉ “ከሀገራችን ላይ እጃችሁን አንሱ” በሚል መሪ ሃሳብ የጀመረውን የተቃውሞ እንቅስቃሴ አጠናክሮ ለአሜሪካ ኤምባሲ እና ለአውሮፓ ኅብረትም በተለያዩ የመረጃ ማስተላለፊያ መንገዶች ተመሳሳይ መልዕክቱ እንዲደርስ ማድረጉን አስታውቆ፣ በእንግሊዝ ኤምባሲ በነበረው ቆይታ ከኤምባሲው የፖለቲካ ቃል አቀባይ እና ካውንስል ጋር የአንድ ሰዓት ውይይት ማድረጉንና መልዕክቱ ለእንግሊዝ መንግሥት እንደሚደርስ ቃል የተገባለት መሆኑንም ገልጿል።

የአውሮፓ ኅብረት ዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ዩታ ዑርፒላይነን፣ በትግራይ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ከዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ጄፍሬይ ፌልትማን ጋር መወያየታቸውንና በውይይቱ በአውሮፓ የሲቪሎች ጥበቃ እና የሰብአዊ ርዳታ የቀውስ አመራር ኮሚሽነር ጃኔዝ ሌናርቺችም እንደተገኙ ትናንት ማምሻውን በትዊተር መልዕክታቸው የገለፁ ሲሆን፣ በዚሁ መልዕክታቸው “ይህን ቀውስ ለመቅረፍ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተቀናጀ አቀራረብ ያስፈልጋል” በማለት አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል፣ የአውሮፓ ኅብረት ዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነሯ በትግራይ ክልል ውስጥ ስላለው ወቅታዊ ኹኔታ በገለጹበት የትዊተር መልዕክት፣ ህብረቱ ምን ለማድረግ እንዳቀደ በግልፅ ያመለከቱን ጉዳይ ባይኖርም “…በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተቀናጀ አቀራረብ ያስፈልጋል” ማለታቸው ህብረቱ የአውሮፓ አገራትን አስተባብሮ “እስከተጨማሪ ማዕቀብ የሚደርስ ተጨማሪ እርምጃ ለመውሰድ ፍላጎት ያለው መሆኑን አመላካች ነው” ተብሎለታል።

LEAVE A REPLY