ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ዛሬ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብርና የህገ መንግስት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የቀረቡትና በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ መዝገብ የተከሰሱ 24 ተከሳሾች ከዛሬ ጀምሮ ጉዳያቸውን ለመከታተል ወደ ፍ/ቤት እንደማይቀርቡ አስታውቀዋል።
ተከሳሾቹ አቤቱታቸውን በጽሁፍ ባቀረቡት የዛሬው ችሎት፣ ንግግር ያደረጉት አቶ ጃዋር፣ የኮሎኔል ገመቹ አያናና የሌሎች ተከሳሾችን ጉዳይ በመጥቀስ “የፍርድ ቤት ውሳኔ በተገቢው መንገድ ተፈጻሚ እየሆነ አይደለም። እኛ እዚህ የመጣነው ከተፈረደብን ለመቀጣት፤ ነጻ ከተባልን ለመውጣት ነው። ከዛሬ ጀምሮ በገዛ ፍቃዳችን ፍርድ ቤት አንቀርብም” ሲሉ ለፍርድ ቤቱ አስታውቀዋል።
በተጨማሪም አቶ ጃዋር፣ በትግራይ ክልል እየተከሰተ ባለው ሁኔታ የትግራይ ህዝብ የረሃብ አድማ ላይ በመሆኑ፤ እነርሱም ለሁለት ቀናት ምግብ እንደማይበሉ ለችሎቱ የተናገሩ ሲሆን፣ ይህንን ውሳኔ የደገፉት አቶ በቀለ ገርባ በበኩላቸው “በግድ ተጎትተን እና ተደብድበን ካልሆነ በቀር ወደዚህ ፍርድ ቤት አንመጣም” ሲሉ ተደምጠዋል።