ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በኬንያው ሳፋሪኮም የሚመራው ጥምረት፣ ከመጪው ዓመት ጥር 2014 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ የሚሰጠውን የቴሌኮም አገልግሎት እንደሚጀምር አስታውቋል።
በዘርፉ አሉ የሚባሉ ስመ ጥር የቴሌኮም ኩባንያዎችንና ተቋማትን በቅንጅት የያዘውና “ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ” የተሰኘው ጥምረቱ ትናንት ግንቦት 16/2013 በይፋዊ ድረ ገፁ ባሰራጨው መግለጫ፣ አላማው በአገሪቱ ላይ የምጣኔ ሀብትና ማኅበራዊ ለውጦችን ለማምጣት እንደሆነ ጠቁሞ “ዋጋው ተመጣጣኝ የሆነ የሞባይልና የኢንተርኔት አገልግሎት በመስጠት ሚሊዮኖች ኢትዮጵያዊያን ጥራት ያለው የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ እፈጥራለሁ” ብሏል።
የሳፋሪኮም፣ ቮዳኮም ግሩፕ፣ ቮዳፎን ግሩፕ፣ የሱሚቶሞ ኮርፖሬሽንና የሲዲሲ ግሩፕ ጥምረት የሆነው እና 850 ሚሊዮን ዶላር በማቅረብ ጨረታውን ያሸነፈው “ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ”፣ በኢትዮጵያ የዲጂታል ሽግግር እውን እንዲሆን ድጋፍ እንደሚያደርግና “የዜጎችንም ሕይወት በበጎ መልኩ እቀይራለሁ” የሚል ተስፋ መሰነቁን በመግለጫው አስረድቷል።