ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ፣ አሸባሪው ህወሓት እስካሁን 22 የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አባላትን መግደሉን አስታውቋል፡፡
የህወሀት ቡድን እስካሁን 20 የሚሆኑ የአስተዳደሩ አባላትን ማገቱንና አራት አባላት ጉዳት ደርሶባቸው ለሕክምና ሆስፒታል መግባታቸውን የገለጸው
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ፣ በአጠቃላይ በ46 የጊዜያዊ አስተዳደር አባላት ላይ ጥቃት መድረሱ በመግለጫው አመልክቷል፡፡
“አሸባሪው ህወሓት መኖሪያ ቤቶችን እያቃጠለና መኖሪያ ቤቶችን በጥይት እየደበደበ ይገኛል። አሁንም ግድያ እና አፈናው በሁሉም አካባቢዎች ቀጥሏል” ያለው መግለጫው፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊትና ጊዜያዊ አስተዳደሩ ክልሉን ለማረጋጋትና አጥፊዎችን ለህግ ለማቅረብ በቁርጠኝነት እየሰሩ እንደሚገኙም ገልጿል።
በሌላ በኩል፣ ከትግራይ ክልል በስምንት መኪናዎች ተጭኖ በህገ ወጥ መንገድ ሊወጣ የነበረ 800 ኩንታል የዕርዳታ እህል፣ አዲ ጉደም ኬላ ላይ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የገለጸው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አሰተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን፣ በድርጊቱ የተሳተፉ ተጠርጣሪዎችን በህግ ጥላ ስር አድርጎ እያጣራ እንደሚገኝም አመልክቷል።
ከዚህ በፊትም በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ሶስት ሺህ ኩንታል የእርዳታ ዕህል መያዙን የገለጸው ፖሊስ “በወንጀል ድርጊቱ የተሳተፉ ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ስር ሆነው ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል” ብሏል።