ሲኖዶሱ አቡነ ማርቆስ ከምስራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት እንዲነሱ ተወሰነ! በመስቀል አደባባይን ጉዳይ ጠንካራ...

ሲኖዶሱ አቡነ ማርቆስ ከምስራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት እንዲነሱ ተወሰነ! በመስቀል አደባባይን ጉዳይ ጠንካራ ውይይት ተደረገ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜናየቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ በትናንት ከሰአት በኋላ ውሎው በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ አጀንዳ ቀርጸው እንዲያቀርቡለት የሰየማቸው ብጹአን አባቶች አዘጋጅተው ያቀረቡለትን የመወያያ አጀንዳዎች መርምሮ ያፀደቀ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት ሰባት የመወያያ አጀንዳዎች፣ የ2013 ዓ.ም የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መወያያ አጀንዳዎች ሆነው መጽደቃቸው ታውቋል።

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ የጸደቁትን ሰባት አጀንዳዎች በቅደም ተከተል እየተወያየ የሚያጸድቃቸው መሆኑን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የአማሮ ቡርጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ የገለጹ ሲሆን፣ የመጀመሪያውንና ሁለተኛውን አጀንዳዎች በከሰአት በኋላ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ተወያይቶባቸው ውሳኔ ማሳለፉንም ጨምረው ገልጸዋል።

በተያያዘ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬ ውሎው፣ ብጹዕ አቡነ ማርቆስ ከምስራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ተነስተው ወደ ጠቅላይ ቤተክህነት ተዛውረው እንዲሠሩ መወሰኑ ታውቋል።

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬ የሁለተኛ ቀን የጉባኤ ውሎው፣ ብጹዕ አቡነ ማርቆስን ከምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት በማንሳት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያና የደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ ሆነው እንዲሰሩ መድቧቸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ፣ ምልአተ ጉባኤው ቀጣዩ የምሥራቅ ጎጃም ሊቀ ጳጳስ ማን ይኹን የሚለውን ጉዳይ በዝርዝር ተመልክቶ ሦስት አጣርተው ማን ይኹን የሚለውን እንዲያቀርቡ (ዘብፁዕ አቡነ አብርሃን፣ ብፁዕ አቡነ ዲዎስቆሮስን እና ብፁዕ አቡነ ኤርምያስን ሰይሞ ከሰዓት ባለው ስብሰባ እንዲያቀርቡ መወሰኑን፤

በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ቆጋ ገዳም ውስጥ ራሳቸውን በራሳቸው “ሊቀ ጳጳስ” አድርገው የሾሙ ሕገ ወጥ የቅብዐት አራማጆችን በማውገዝ “አቶ” ተብለው እንዲጠሩም መሰየሙን፤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እስከ ጥቅምት 2014 ዓ.ም ድረስ ምንም ዓይነት ቅጥር፣ ዝውውር፣ ዕድገት እንዳይሠራ ማዘዙን ከኢኦተቤክ ህዝብ ግንኙነት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

በዚሁ ምልአተ ጉባኤ መስቀል አደባባይን በተመለከተ ጠንካራ ውይይት መደረጉንና መንግሥትን በደብዳቤ የመጠየቅ ስምምነት ላይ ስለመደረሱም ከውስጥ አዋቂ ምንጮች በደረሰን መረጃ ተጠቁሟል።

LEAVE A REPLY