ቦርዱ ለ2 ዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢዎች እውቅና ሰጠ! የምርጫ ፖስተር የቀደደው በእስር...

ቦርዱ ለ2 ዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢዎች እውቅና ሰጠ! የምርጫ ፖስተር የቀደደው በእስር ተቀጣ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜናየኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከዓለም አቀፍ ሪፕብሊካን ኢንስቲትዩት (IRI) ለዓለም አቀፍ የዴሞክራቲክ ኢንስቲትትት (NDI) የምርጫ ታዛቢ ቡድን የምርጫ መታዘብ እውቅና መስጠቱን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመንግስት ግብዣ መሰረት 6ተኛው አገር አቀፍ ምርጫ በጋራ ለመታዘብ ለሚሰሩት ለዓለም አቀፍ ሪፕብሊካን ኢንስቲቲዩት (IRI) ለዓለም አቀፍ ዴሞክራቲክ ኢንስቲትዩት (NDI) የምርጫ መታዘብ እውቅናን ሰጥቷል።

ቦርዱ የድርጅቶቹ የጋራ የታዛቢ ቡድን ያቀረበውን የጥናት ዘዴ በማየት፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ታዛቢዎች መሰረታዊ መርህዎችን እና የታዛቢዎች አለም አቀፍ የስነምግባር ደንብ በተከተለ መልኩ እንደሚሰሩ ስምምነት ላይ በመድረስ ነው የመታዘብ እውቅናውን የሰጠው።

በኮቪድ ወረርሽኝ የተነሳ የታዛቢ ቡድኑ የሚያከናውነው የመታዘብ ተግባር የስፋት ውስንነት እንደሚኖረውና ይህንንም በሚያደርጋቸው ስራዎች እና ማጠቃለያዎች ላይ የሚገልጽ መሆኑን ታዛቢ ቡድኑ እና ቦርዱ በጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል ተብሏል። ቦርዱ ከዚህ በፊት ለ45 የአገር ውስጥ የምርጫ ታዛቢዎች እውቅና መስጠቱም በዛሬው መግለጫው አስታውሷል።

በሌላ በኩል፣ የምርጫ ማስታወቂያ የቀደደ ግለሰብ በእስራት መቀጣቱ የተገለፀ ሲሆን፣ በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የጋንታ መይጨ ቀበሌ ነዋሪ የሆነው የ44 ዓመቱ ደርጉ እማኔ፣ ግንቦት 12 ከቀኑ 11፡00 ሰዓት አካባቢ ንብረትነቱ የብልፅግና ፓርቲ የሆነውን የምርጫ ምልክት አምፖል ፖስተር ከተሰቀለበት ቦታ ቀዶ በመጣሉ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ 1162/2013 ስር አንቀፅ 158 የምርጫ ማስታወቂያ ማጥፋት የተደነገገውን ክልከላ በመተላለፍ መከሰሱን የጋሞ ዞን ኮሚኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል።

በዚህም፣ ተከሳሹ ድርጊቱን ስለመፈጸሙ ሶስት የዐቃቤ ሕግ የሰው ማስረጃዎች በመመስከራቸውና ተከሳሽ የመከላከያ ማስረጃ ማቅረብ ባለመቻሉ፣ የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ፍ/ ቤት ልዩ የምርጫ ችሎት ባስቻለው ችሎት፣ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ከመሰል ድርጊት እንዲቆጠቡ ያስተምራል ተከሳሹን ያርማል ያለውን የ2 ወር ቀላል እስራት እንዲቀጣ ግንቦት 17/2013 መወሰኑን ቢሮው ገልጿል፡፡

የአርባንጭ ዙሪያ ወረዳ ዐቃቤ ህግ ጽ/ቤት “ማንኛውም ሰው የእጩ ተወዳዳሪ፣ አባል እና ደጋፊ ፖስተር ወይም የምርጫ ማስታወቂያ ያበላሸ፣ ያስወገደ፣ የቀደደ እንደሆነ የወንጀል ተጠያቂነት ይከተለዋል፤ ህብረተሰቡም ከመሰል ድርጊቶች ሊቆጠብ ይገባል” የሚል መልዕክት ማስተላለፉንም የጋሞ ዞን ኮሚኒኬሽን ቢሮ አመልክቷል።

LEAVE A REPLY