ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የሱዳን ታጣቂዎችና በሱዳን ይደገፋሉ የተባሉ የኢትዮጵያ አማፂያን፣ ምዕራብ ጎንደር የእርሻና የከብት ማርቢያ ማዕከላትን ማቃጠልና መዝረፋቸውን ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች አመልክተዋል።
የሱዳን ታጣቂዎችና ሌሎች በሱዳን ኃይሎች የሚታገዙ አካላት በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ቱመት መንዶካ በተባለ ቀበሌ፣ ከባለፈው እሁድ ጀምሮ ጥቃት ማድረሳቸውን፣ ንብረት መዝረፋቸውንና ማቃጠላቸውን የአካባቢው የግብርና ባለሀብቶች፣ ነዋሪዎችና የቀበሌው አስተዳደር ያስታወቁ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግስትም ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህም የሱዳን ታጣቂዎች በምዕራብ አቅጣጫ ድንበር ተሻግረው ወደ ኢትዮጵያ ግዛት በመግባት ጥቃቶችን በማድረስ ዘረፋ እንደሚፈፅሙና ንብረትም እንደሚያቃጥሉ በተደጋጋሚ ሲገልፅ ቆይቷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ከሱዳን ሰልጥኖ የገባው መሆኑ የተነገረለትና ሰሞኑን በጎንደርና አካባቢው ሰው ሲያግት፣ ገንዘብ ሲሰበስብና ጥይት ሲተኩስ የሰነበተ የትህነግ አሸባሪ ኃይል፣ በትናንትናው ዕለት በቁጥጥር ስር መዋሉ ተነግሯል።
የመከላከያና የክልሉ ልዩ ሀይል ዛሬ ባደረጉት አሰሳም ከጎንደር ወጣ ብለው በተሰሩ ሕገወጥ ቤቶችና አካባቢው የዚህ የሽብር ቡድን በርከት ያሉ አባላት በቁጥጥር ስር የዋሉ መሆናቸውና ከዚህ ኃይል መካከል አብዛኛዎቹ የትግራይ ተወላጆችና ቀሪዎቹም በአካባቢው በማንነት ሰበብ ለትህነግ የሚላላኩ እንደሆኑ ተመልክቷል።
ይህ ቡድን ዱቄት፣ ዘይት፣ ስኳርና ሌሎች ስንቆችን ከጎንደር ከተማ ወጣ ብለው በሚገኙ ሕገወጥ ቤቶች አከማችቶ፣ የሽብር ቡድን አባላቱን በሕገ ወጥ ቤቶቹ አስጠልሎ፣ ከበርካታ ጥይቶች፣ የቡድንና የነፍስ ወከፍ መሳርያዎች ጋር መያዙም ተነግሯል።
መንግስት ከአንድ ወር በፊት፣ ከሱዳን የገባው የትህነግ ኃይል ጭልጋ አካባቢ መከላከያ ሰራዊቱ ላይ ጥቃት ከፈፀመ በኋላ እርምጃ እንደተወሰደበት መግለጹ ይታወሳል።