‹‹አይገጥምም›› አልሽ አሉ፤
‹‹እንዳስጣለች ላም ግት፣ ብእሩ ነጠፈ፤
እንደ ሾላ ፍሬ፣ ምናቡ ረገፈ፡፡››
አልሽ አሉ፡፡
.
‹‹ይመጥቅ የነበረ፣
ይቀኝ የነበረ፣
በአእዋፍ ዝማሬ፤
ወፎች ሲዘምሩ፤
ያቃዠዋል ዛሬ፡፡››
አልሽ አሉ፡፡
‹‹እንደ አዞ ገላ፣ ስሜቱ ከርድዷል፤
እንዳለፋ ቆዳ፣ ምናቡ ቆርፍዷል፡፡
የምንጭ መንፎልፎል፤
ማእበል የሰበቀው፣ የባህር መገንፈል፤
አድማስ ላይ የረጋ፣
. . . . . . የምሽት ተቅላሎት፤
ጉም ላይ የተጠለፈ፣
ተራራ የታጠቀው፣
. . . . . . የማርያም መቀነት፤
ዳመና የሚቀድ፣
መብረቅ የገመደው፣
. . . . . . . የብርሀን ሰንሰለት፤
አይፈነቅለውም!
ለውበት ደንቁሯል፤
ለእውነት ታውሯል፡፡››
አልሽ አሉ፡፡
.
አልዋሸሽም ፍቅሬ፣
አንቺን ልቤ ድርጌ፣
. . . . . አለምን ዘርፌያት፤
እንኳን የምቀኘው፣
የማየው ምን አላት?!
————
ግንቦት፣ 2013