ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የመከላከያ የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር ብ/ጄ ቡልቲ ታደሰ፣ ከአሚሶም ኃይል አዛዥ ሌ/ጄ ዳዮመንዴ ንደገያ ጋር በመሆን በሶማሊያ ስላለው ወቅታዊ የሠላም ማስከበር ሁኔታና ተያያዥ ጉዳዮች፣ ከኢፌዴሪ መከላከያ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ጋር ውይይት አደረጉ።
የፀጥታ ኃይሉ እየወሰደ ባለው ዕርምጃ አልሸባብ እየተዳከመ መሆኑንና በተለያዩ ቀጣናዎች ያቀዳቸው የሽብር ተልዕኮዎች መክሸፋቸው ተገለጿል።
በምክክሩ ወቅት የመከላከያ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላ ፣ በቀጣናው ሠላምን ለማስፈን ቅንጅታዊ አሠራሮችን አጠናክሮ ማስቀጠል እና ዘላቂ ሠላምን ለማስፈን የሶማሊያ ፀጥታ ኃይልን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ የተናገሩ ሲሆን፣ የአሚሶም ኃይል አዛዥ ሌ/ጄ ዳዮመንዴ ንደገያ፣ የኢትዮጵያ ጦር አልሸባብን በመዋጋት እያሳየ ያለውን ጀግንነት አድንቀው “ቀጣናውን ሠላማዊ ለማድረግ ቅንጅታዊ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ጦር አሁን ላይ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ አልፎ፣ ወደ ሶማሊያ በመዝመት ዓለም አቀፍ አሸባሪ በሆነው አልሸባብ ላይ የኃይል ዕርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ የገለፀው የመከላከያ ሰራዊት ሚዲያ፣ የመከላከያ የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ብ/ጄ ቡልቲ ታደሰ፣ በሚወሰድበት ዕርምጃ አልሸባብ እየተዳከመ መሆኑን፣ ያቀዳቸው የሽብር ተልዕኮዎች መክሸፋቸውንና ሰራዊታችን ቀጣናውን ከአሸባሪው ኃይል እያፀዳ እንደሚገኝ መግለፃቸውን አመልክቷል።