ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የሐርቫርድ ቲ.ኤች ቻን የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት፣ ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በታች ለሆኑና “በጠንካራ ራዕያቸው እና ተነሳሽነታቸው በዓለም አቀፍ የጤና ኢኖቬሽን ላይ የራሳቸውን አሻራ ያሳረፉ ወጣቶች” በሚል በየአመቱ የሚሸልም ሲሆን፣ የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰንም የዘንድሮ (2021) የኔክስት ጄኔሬሽን ሽልማት አሸናፊ አድርጓቸዋል።
በቨርቹዋል (ኢንተርኔት) በተካሄደው የሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ
ለዶ/ር ሊያ ሽልማቱን ያበረከቱት የፋኩልቲው ዲን ሚሼል ኤ. ዊሊያምስ ባደረጉት ንግግር “ዶ/ር ሊያ ለሽልማቱ የበቁት በተለይ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር በወሰዷቸው ወሳኝ እርምጃዎች ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
“በዚህ የኮቪድ-19 በፈጠረው ውጥረት ውስጥ ለምትገኘው ዓለማችን እንደዚህ ዓይነት ወጣቶች ከምንጊዜውም በላይ አስፈላጊ ናቸው” ያሉት የፋኩልቲው ዲን “እስካሁን ካወቅኳቸው ግለሰቦች መካከል ዓለምን መቀየር ለቻለችዋ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ይህን ሽልማት ሳቀርብ ክብር ይሰማኛል” ብለዋል።
“በየትኛውም የዓለም ሀገራት ውስጥ የጤና ዘርፉን መምራት እጅግ ፈታኝ ነው። ዶ/ር ሊያ ግን በኢትዮጵያ የጤና ሚኒስትርነትን ከያዙበት ቀን አንስቶ በተለይ በፈታኙ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ሥራቸውን በብቃት የተወጡ ናቸው።
ኮቪድ-19ን ከመከላከል እና ከመቆጣጠር አንፃር በመንግሥት እና በግል ባለሃብቶች መካከል፣ በሀገሪቱ የጤና ባለሙያዎች እና በዓለም አቀፍ በጎ አድራጊ ድርጅቶች መካከል እንዲሁም በምሁራን እና በሌሎች ኢትዮጵያውያን መካከል የፈጠሩት አንድነት እና አብሮነትም የሚያስደንቅ ነው” በማለትም ሚሼል ኤ.ዊሊያምስ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
ከሽልማቱ በኋላ ንግግር ያደረጉት ዶ/ር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው፣ የሐርቫርድ ቲ.ኤች ቻን የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት ለዚህ የከበረ ሽልማት የመረጣቸው በመሆኑ የተሰማቸውን ክብር ገልጸዋል።