ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ላለፉት ሁለት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን ስብሰባ መጠናቀቅ አስመልክቶ ባስተላለፈው መልዕክት “ብዙ ሀገራት ከሌላ የዓለም ዳርቻ መጥተው በቀይ ባሕር ዙሪያ የጦር መንደሮችን ከመመሥረት፣ ወደቦችን ከማልማት፣ የንግድ መሥመሮችን ከመዘርጋት ባለፈ፣ በቀጣናው ፖለቲካ ላይ እጃቸውን ከማስገባት ተቆጥበው አያውቁም። ኢትዮጵያ ደግሞ ከቀይ ባሕር ጋር አብራ የተፈጠረችና የኖረች ሀገር ናት” ብሏል።
“ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትገኝበት ጂኦ ፖለቲካዊ ከባቢ ዛሬም እንደ ትናንቱ የዓለም ዓይን ማረፊያ ሆኖ ይገኛል። ከሜዲትራንያን ባሕር ቀጥሎ በዓለም ታሪክ ላይ በሚደረጉ የንግድና ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎች የሚጠቀሰው ቀይ ባሕር ነው። በዚህ ቀጣና ላይ የበላይነት መያዝ በዓለም አቀፍ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ይታመናል” በማለት ዝርዝር ጉዳዮችን የሚዳስሰው የፓርቲው መልዕክት ከጥንት ጀምሮ በቀይ ባሕር ሲደረግ በነበረው ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ እና የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ጉልሕ ሚና ነበራት። የእኛን ተሳትፎ ከሌሎቹ ሀገራት ለየት የሚያደርገው የፍላጎታችን ምንጩ ከቀይ ባሕር ጋር ካለን ቅርበት ጋር የተያያዘ መሆኑ ነው። ብንፈልግ እንኳን ከቀይ ባሕር ፖለቲካ ልናመልጥ አንችልም። እንደ መጥፎ ዕድል ሆኖ አንዳንድ አካላት ቀይ ባሕር ላይ ያላቸው ፍላጎት የሚሳካ የሚመስላቸው ሀገራችን ስትዳከም ነው። ይኼ ደግሞ እንደ ሉዓላዊ ሀገር በፍጹም ተቀባይነት የለውም” ሲል አስታውቋል።
የሀገራችንን ጥቅም በኃይል ወይም በዲፕሎማሲ ተጽዕኖ የማጣት ምንም ዓይነት ፍላጎት እንደሌለን መታወቅ እንዳለበት የጠቀሰው ፓርቲው “እኛ እንደ ሀገር ከቀይ ባሕር ጥቅም ለማግኘት ስናቅድ ከሁሉም ጎረቤቶቻችን ጋር በሰጥቶ መቀበል መርሕ ተስማምተን እንጂ፣ ከማናቸውም ጋር እሰጣገባ ውስጥ በመግባት አይደለም። የጋራ ፍላጎቶቻችንን በጋራ ለማሳካት ተግባብተን፣ በሰላማዊ መንገድ እንደምንሠራ የዲፕሎማሲ ታሪካችን ምሳሌ መሆን ይችላል።
ሌላው ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር አካባቢ ካላት ጂኦ ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ባለፈ የዓባይ ዋና ምንጭ በመሆኗም የአፍሪካን ቀንድና የሰሜን ምሥራቅ አፍሪካን ሁኔታ የመወሰን ዐቅም አላት። ከግሪክ ሥልጣኔ ዘመን ጀምሮ አውሮፓውያንና እስያውያን ኢትዮጵያን ለማግኘት ከተጉበት ምክንያቶች አንዱ የዓባይን ምንጭ ለማወቅና ለመቆጣጠር እንደሆነ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ። በእነዚህ በሁለቱ ጂኦ ፖለቲካዊ ምክንያቶች የተነሣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ፣ ብሎም በአፍሪካ አህጉር ደረጃ ጠንካራ እየሆነች ከመጣች ጥቅማቸው የሚነካ የሚመስላቸው አካላት ሥጋት ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ ግልጽ ነው” ብሏል።
ከዚሁ ጋር በማያያዝም “መታወቅ ያለበት ሐቅ፣ ድሮም ሆነ ዛሬ ኢትዮጵያ የሌሎች ጥቅም ላይ ምንም ዓይነት ሥጋት የመፍጠር ዓላማ የላትም። በተመሳሳይ የሀገራችንን ጥቅም ላይ ሌሎች ተጽዕኖ እንዲፈጥሩብን አንሻም።… ከኤርትራ ጋር ያለን ግንኙነት መታደሱና በአጠቃላይ በቀጣናው ላይ የፈጠርነው መልካም ግንኙነትና ትሥሥር ቀጣናውን ለሚታዘቡ ኃይሎች ደስ የሚያሰኛቸው ጉዳይ እንዳልሆነ እሙን ነው።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በቅርቡ ከሱዳን ጋር የገባችበት ሁኔታ ከነበረን መልካም የሆነ የረጅም ዘመናት ግንኙነት አኳያ ሲፈተሽ ፈጽሞ መፈጠር የሚገባው እንዳልሆነ ግልጽ ነው። አሁንም ቢሆን ለዘመናት የቆየ በጎ ግንኙነት ታሳቢ በማድረግ በድንበር አካባቢ የተፈጠረውን ችግር በሰላማዊ ሁኔታ ለመፍታት እንሠራለን… የኢትዮጵያን ሥልጣኔ ማየት የማይሹ አካላት ዋናው ዓላማቸው ደካማ ኢትዮጵያን መፍጠር ነው። ለዚህ ደግሞ ሦስት መንገዶችን ይጠቀማሉ። ኢትዮጵያን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ከጎረቤቶቿ ጋር በጦርነት መማገድ፣ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ማዳከም እና ኢትዮጵያውያንን በአካባቢና በእምነት ማጋጨት ናቸው። ከጥንት ዘመናት ጀምሮ ኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠሩ ጦርነቶችን ከባዕድ ወራሪዎች ጋር አድርጋለች።
የእነዚህ ጦርነቶች ዋና ዓላማ ሀገሪቱ ፋታ አግኝታ የሥልጣኔ መንገዶቿን እንዳትከተል ማድረግ ነው። በእርግጥም ጦርነቶቹ በተወሰነ አዳክመውን አልፈዋል። ከጦርነቱ ባሻገር የኢትዮጵያን የንግድ መሥመሮች በመያዝ፣ ከባሕር በር ውጭ በማድረግ እና ዓለም አቀፍ ብድርና ርዳታ አግኝታ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን እንዳታካሂድ ዕንቅፋት በመፍጠር የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማሰናከል ጥረት ተደርጓል። የዓባይ ግድብንም ሆነ ሌሎች ግድቦችን ለመገንባት ኢትዮጵያ በታሪኳ ያደረገቻቸው ጥረቶች ያልተሳኩበት አንዱ ምክንያት ይኼ ነበር” ሲል ፓርቲው አመልክቷል።
ከዓባይ ወንዝ ተገቢውን ጥቅም ማግኘት እንዳንችል ካደረጉን ምክንያቶች መካከል ለፕሮጀክቶቹ ማስፈጸሚያ የሚውል ገንዘብ እጥረት፣ የእርስ በርስ ጦርነት እና የዓለም ፖለቲካ ተለዋዋጭ አሠላለፍ የሚጠቀሱ መሆናቸውን ያነሳው ይኸው የብልጽግና ፓርቲ መልዕክት፣ አንድ አንድ ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ በጎረቤት ሀገራት የሚቃጡ ጦርነቶችን በመቆስቆስና በመደገፍ፣ በሀገር ውስጥ የፖለቲካ ዐማጽያንን በመደገፍና የእርስ በርስ ጦርነትን በማቀጣጠል፣ ለጋሽ ሀገራት የገንዘብ ድጋፍ እንዳያደርጉ በመጎትጎት፣ ወዘተ. ዓባይን እንዳንጠቀም የሚቻላቸውን ሁሉ ሲያደርጉ እንደነበረም ገልጿል።
“የእምነትና የብሔር ልዩነቶቻችንን እንደ ጸጋ ብቻ በመቁጠር፤ አንድ ሆነን እንደ ብዙ፤ ብዙ ሆነን እንደ አንድ በመንቀሳቀስ፤ የጀመርናቸው ፕሮጀክቶች ሁሉ በተገቢው ደረጃና ፍጥነት በማጠናቀቅ፤ ከቃል ይልቅ ለተግባር ቅድሚያ በመስጠት፤ የመከላከያ ኃይላችንን በሙሉ ዐቅም በመደገፍ፤ የፖለቲካ አመራራችንን በሀገራዊው ተልዕኮ ላይ እንዲያተኩር በማድረግ፤ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ዲፕሎማቶቻችን ሀገራችንን በዓለም መድረክ በብቃት መወከላቸውን በማስከበር – ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ኢትዮጵያን መውደዳቸውን በአመቺ መንገዶች ሁሉ እየገለጹ፣ ከኢትዮጵያና ከሕዝባቸው ጎን መሆናቸው በማሳየት – በኢትዮጵያዊነት ስሜት አንድ ሆነው እንዲቆሙ ጥሪ እናደርጋለን” ሲልም ፓርቲው መልዕክት አስተላልፏል።
በተያያዘ፣ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የብልፅግና ፓርቲ ሊቀ መንበሩ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በይፋዊ የፌስ ቡክ ገፃቸው “የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባችንን ለ ኢትዮጵያ ሰላምና ብልፅግና ቁርጠኝነታችንን በማደስ አጠናቅቀናል” ሲሉ ከሰዓታት በፊት አሰታውቀዋል።