ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደና ሜ/ጄነራል አበበ ተ/ሀይማኖትን ጨምሮ የሽብርተኛው ህወሓት አባላት ላይ የንብረት...

ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደና ሜ/ጄነራል አበበ ተ/ሀይማኖትን ጨምሮ የሽብርተኛው ህወሓት አባላት ላይ የንብረት እግድ ተጣለ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜናአዲስ አበባ የሚገኙ ቋሚ ንብረቶቻቸውን በቤተሰቦቻቸውና በወኪሎቻቸው አማካኝነት በማከራየትና ከፍተኛ ገቢ በመሰብሰብ ለሽብር ተልዕኮ እያዋሉ ባሉ የሽብርተኛው የህወሓት ቡድን አባላት ላይ የንብረት እግድ የተጣለ መሆኑን የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ።

በተመሳሳይ ሸብርተኛውን የሸኔ ቡድን በገንዘብ ሲደግፉ የነበሩ የ141 ተጠርጣሪ ግለሰቦች የፋይናንስ ስርዓት እንዲቋረጥና ገንዘባቸው እንዲታገደ መደረጉንም የጋራ ግብረ ኃይሉ አመልክቷል፡፡

የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል፣ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በአሁኑ ወቅት ከሽብርተኛው የህወሓት ቡድን ጋር ተሰልፈው ሀገር ለማተራመስና ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱት ግለሰቦች፤ ቀደም ሲል ለህዝብና ለሀገር ጥቅም እንዲሰሩ የተጣለባቸውን ከባድ ሀላፊነት ወደ ጎን በመተው ከፍተኛ ሃብት በመመዝበር በአዲስ አበባና በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ንብረቶች አፍርተዋል፡፡

በፈፀሙት የሀገር ክህደት ወንጀል የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ ወጥቶባቸው እንደነበርም መግለጫው፣ እነዚህ ግለሰቦች በአንድ በኩል በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሽብር ጥቃቶችን በመፈጸም፣ ግጭትና ትርምስ ለመፍጠር ከሚንቀሳቀሰው የህወሓት የጥፋት ቡድን ጋር በአመራርነትና በአባልነት እየተሳተፉ መሆኑን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከህዝብና ከሀገር በመዘበሩት ሃብት በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች የገነቧቸውን የመኖሪያ ህንፃዎችና ያቋቋሟቸውን የንግድ ድርጅቶች፣ በቤተሶቦቻቸውና በወኪሎቻቻው አማካኝነት በማከራየት በወር እስከ 9ሺህ ዶላር ድረስ ሲሰበስቡ መቆየታቸውን አመልክቷል፡፡

“ግለሰቦቹ ይህን ከኪራይ የሚገኝ ከፍተኛ ገቢ በህገወጥ መንገድ በመላክ የሽብር ቡድኑን ህልውና ለማስቀጠል ለተለያዩ የጦር መሣሪያዎችና ጥይቶች ግዢ እንዲሁም ለሎጀስቲክስ አቅርቦት ከማዋል ባሻገር ንብረቶችን በመሸጥም ጭምር ሃብት የማሸሽ ስራ ለመስራት እየተንቀሳቀሱ እያሉ በተደረገባቸው ጥብቅ የመረጃ ስራና ክትትል ማስረጃዎችን በማሰባሰብ ለሚመለከተው የመንግስት አካል በማቅረብ እግዱ በፍርድ ቤት በኩል እንዲፈጸም ተደርጓል” ያለው መግለጫው፣ ንብረታቸውን እንዳያንቀሳቅሱና እንዲታገድ የተደረገባቸው የሸብርተኛው የህወሓት ቡድን አመራርና አባላት ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ በቅፅል ስሙ ወዲ ወረደ፣ ሌተናል ጄነራል ፍስሃ ኪዳኑ በቅፅል ስሙ ፍስሃ ማንጁስ፣ ሜጀር ጄነራል አበበ ተ/ሀይማኖት በቅፅል ስሙ ጆቤ፣ ሜጀር ጄነራል ሀልፎም እጅጉ በቅፅል ስሙ ወዲ እጅጉ፣ ሜጀር ጄነራል ተስፋዬ ግደይ፣ ብርጋዴር ጄነራል ሃ/ስላሴ ግርማይ በቅፅል ስሙ ወዲ እንቤተይ፣ ብርጋዴር ጄነራል ምግበ ሀይለ፣ ብርጋዴር ጄነራል ተክላይ አሸብር በቅፅል ስሙ ወዲ አሸብር፣ አቶ ኢሳያስ ወ/ጊዮርጊስ፣ አቶ ሀሰን ሽፋ በድምሩ አስራ ዘጠኝ (19) መሆናቸውን ገልጿል።

መግለጫው አክሎም፣ መቀሌ ከተማ ሆነው ለሽብር ቡድኑ መረጃ ሲሰጡ የፋይናንስና የሎጀስቲክስ ድጋፎችን በድብቅ ሲያቀርቡ እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊት የደንብ ልብሶችን በመልበስ በጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮችና ሰራተኞች ላይ ተመሳስለው ጥቃት ሲፈጽሙ ከነበሩ ግለሰቦች መካከል 14 የቡድኑ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቅሷል፡፡

“እነዚህ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት፣ ለሰብአዊ ድጋፍ በመጓጓዝ ላይ የነበሩና እያንዳንዳቸው 20 ሌትር የምግብ ዘይት የያዙ 2200 ጄሪካኖችን የጫነ አንድ ተሽከርካሪ ከእነ ተሳቢው አስገድደው አቅጣጫውን እንዲቀይር በማድረግ በድብቅ ለሽብር ቡድኑ ለመላክ ሲሞክሩ ነው” ሲል የሚያትተው የግብረ ኃይሉ መግለጫ፣ በተመሳሳይም ሀገር በማፍረስ ሴራ ውስጥ በመሳተፍ ላይ ያለውን የአሸባሪውን የሸኔ ቡድንን እንቅስቃሴ በገንዘብ ሲደግፉ የነበሩ የ141 ተጠርጣሪ ግለሰቦች የፋይናንስ ስርዓት እንዲቋረጥና በአካውንታቸው ውስጥ የተገኘ ከፍተኛ ገንዘብ እንዲታገደ መደረጉንም አመልክቷል፡፡

በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞኖች፣ በጅማና በዙሪያው በሚገኙ ወረዳዎች 27 አባላቱም በጸጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን ያመለከተው የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይሉ፣ ለቡድኑ ሊላኩ የነበሩ በርካታ የጦር መሳሪያዎችና ጥይቶችም በተደረጉ ጥብቅ ክትትሎች በተለያዩ አካባቢዎች መያዛቸውንና አሸባሪው ሸኔ ባዋቀራቸው ሴሎች ዙሪያ ይደረግ በነበረው ክትትል ለቡድኑ ተገዝተው ሊላኩ የነበሩ 5661 (አምስት ሺህ ስድሰት መቶ ስልሳ አንድ) የክላሽንኮቭ ጥይቶች፣ 2000 (ሁለት ሺህ) የብሬን መትረየስ ጥይቶች፣ ሌሎች ለጥፋት ተልዕኮ መፈፀሚያ የሚውሉ ቁሶችና ሰነዶች እንዲሁም አዘዋዋሪዎቹም ጭምር ቡራዩ፣ ጊንጪና ከአምቦ ወጣ ብላ በምትገኘው ባቢች በተባለች ቦታ ላይ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቋል።

የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይሉ፣ ለሸብርተኞቹ የህወሓትና የሸኔ ቡድን አባላት የሽብር ተግባር የሚውሉ ህገወጥ ገንዘቦችን ምንጭ በተመለከተ ባደረገው ሚስጥራዊ ክትትል ሰሞኑን በአዲስ አበባ ቦሌ ኤርፖርት እንዲሁም በቶጎ ውጫሌ እና በሌሎችም አካባቢዎች ጭምር በህገወጥ መንገድ ሊወጡ የነበሩ የተለያዩ ሀገራት የብር ኖቶች በቁጥጥር ስር ማዋሉውንም በመግለጫው ጠቁሞ፣ በተደረገው ጥብቅ ክትትልና ፍተሻም አንድ ሚሊዮን 267 ሺህ የአሜሪካ ዶላር፣ ከ900 ሺህ በላይ ዩሮ፣ እንዲሁም 90ሺህ ፓውንድና ከ2 ሚሊዮን በላይ የኢትዮጵያ ብር ከአስራ ሁለት ተጠርጣሪዎች ጋር መያዙን አመልክቷል፡፡

በተያያዘ፣ ሰሞኑን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተቀሰቀሰውን ግጭት እንደ መልካም አጋጣሚ በመቁጠርም መነሻውን ጋምቤላ መዳረሻውን አማራ ክልል በማድረግ በታርጋ ቁጥር ኮድ 3 አ/አ A25773 አይሱዝ የጭነት መኪና የታሸጉ ውሃዎችንና ሸቀጦችን እንደሽፋን በመጠቀም ሚስጥራዊ ቦታ በማዘጋጀት 62 ክላሽንኮቭ ከ36 ካዝናዎች ጋር በድብቅ ለማሳለፍ የሞከሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መግለጫው አመልክቷል፡፡

በመጨረሻም፣ ሽብርተኞቹ የህወሓትና የሸኔ ቡድን አባላት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለመፈፀም የሚሞክሯቸው ጥቃቶች እንዲሁም በውጭ ጸረ ኢትዮጵያ ኃይሎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች፣ ግጭትና ትርምስ በመፍጠር የኢትዮጵያን ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል ያለሙ መሆናቸውን መላው ህብረተሰብ በመገንዘብ ሴራዎቹን በማክሸፉ ሂደት ከጅምሩ ጥቆማ በመስጠትና ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ላበረከተው አስተዋፅኦ የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ሃይሉ ምስጋናውን ያቀረበ ሲሆን፣ በቀጣይም የጥፋት ተልዕኮዎቹን ለማክሸፍ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተሳትፎው ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ህብረተሰቡም በአካባቢው አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከት ለጸጥታና ለመረጃ አካላት የተለመደ ጥቆማ መስጠቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፏል፡፡

ሽብርተኞችን በገንዘብ የሚደግፍ ማንኛውም አካል ጉዳዩ በህግ የሚያስጠይቅ መሆኑን ሊገነዘብ እንደሚገባ የጠቆመው የጋራ ግብረ ሃይሉ መግለጫ፤ የሀገርን ሉዓላዊነትና አንድነት አስጠብቆ ለመዝለቅ በሽብርተኞቹ የህዋሓትና የሸኔ ቡድን አባላት የሚቃጣውን ጥቃት እንዲሁም በውጭ ፀረ ሰላም ሀይሎች የሚቀነባበረውን ሴራ ለማክሸፍ በደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል እየተወሰደ ያለውን የተቀናጀና ተከታታይ እርምጃ በመገናኘ ብዙሃን በኩል ለህብረተሰቡ ይፋ የማድረግ ሂደቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጧል፡፡

LEAVE A REPLY