ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር፣ በኢትዮጵያ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ላይ የጣለውን የቪዛ ክልከላ፣ በአሜሪካ ሴኔት ፊት በግልጽ የተቃወሙትና ማዕቀቡ ተገቢነት እንደሌለው በመግለጽ ከኢትዮጵያ ጎን የቆሙት፣ የኦክላሃማው ሴናተር ጂም ኢንሆፍ አዲስ አበባ ገብተዋል።
በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍና በአሜሪካ ሴኔት ፊት ባቀረቡት ሰፊ ሪፖርት፣ አሸባሪውን ህወሓትና የኢትዮጵያ መንግስትን በእኩል ዓይን መመልከት ተገቢነት የሌለው መሆኑን አጥብቀው በመቃወም፣ የባይደን አስተዳደር ያሳለፈው ውሳኔ ለችግሩ ሰላማዊ መፍትሄ ለመስጠት በመንግስት በኩል እየተደረገ ላለው ጥረት የሚፈይደው ነገር እንደሌለ በግልጽ ያስታወቁት የሪፐብሊካን ፓርቲ ሴናተር ሴም ጂም ኢንሆፍ፣ ዛሬ አዲስ አባበ የገቡ ሲሆን፣ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድም በፌስቡክ ገፃቸው “የኢትዮጵያውያን ወዳጅ የሆኑትን፣ የዩናይትድ ስቴትስ ሴናተር፣ ጂም ኢንሆፌን ወደ ሁለተኛው ቤትዎ #ኢትዮጵያ እንኳን ደኅና መጡ እላለሁ” የሚል መልእክት አስተላልፈዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ አንዳንድ አገሮች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት በመቃወም “ድምፃችን ለነፃነታችንና ለሉዓላዊነታችን” በሚል መሪ ሐሳብ ትናንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል።
በዋናነት አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ያሳለፈችው የጉዞ እገዳና የኢኮኖሚ ማዕቀብ ውሳኔ የተሳሳተ መሆኑን ባስገነዘበውና በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ፣
“ሕዳሴ ግድቡ የፍትሐዊነት ማሳያ ነው፣ መሪዎቻችንን እኛው እንመርጣለን፣ ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷ እና በነጻነቷ ትቀጥላለች፣ የሕዳሴ ግድቡ ሁለተኛ የውኃ ሙሊት የመንግሥት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያውያንም ነው” የሚሉ እና ሌሎች መልእክቶች በአማርኛ፣ በእንግሊዘኛና በአረብኛ ቋንቋዎች የተላለፉ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ የሕዳሴ ግድቡ ድርድር አፍሪካዊ መፍትሔ እንዲያገኝ ድጋፍ እየሰጡ የሚገኙ እና ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ግንኙነት አላቸው የሚባሉት የቻይና፣ የሩሲያና የቱርክ መሪዎንች ምስልም ሰልፈኞቹ ይዘው ወጥተዋል።
በተያያዘ፣ በኢትዮጵያ ላይ የውጭ ኃይሎች እያደረጉትን ያለውን ጣልቃ ገብነትና ጫና ለመመከት እንደሚሠሩ በተለያየ የአለም ክፍል የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የተቃውሞ ሰልፍ በማካሄድ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ የመንግሥትን አቋም በመደገፍ የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉ ያለውን ጣልቃ ገብነትና ጫና በመቃወም በጣሊያን ሮም ከተማ ሰልፍ ያካሄዱ ሲሆን፣ በኖርዌይ ኦስሎና አካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ላይ ያስተላለፈውን ውሳኔ በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄዳቸውና በካናዳ አልበርታ ግዛት በካልጋሪ፣ ሌትብሪጅና ፎርትማክመሪ የሚኖሩ ኢትዮ – ካናዳውያን የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የጣለውን የጉዞና ተያያዥ ማዕቀብ በካልጋሪ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ በማካሄድ መቃወማቸው ታውቋል።