ሴናተር ጂም ኢንሆፍና የኢትዮጵያ መንግሥት ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸው ተገለጸ!

ሴናተር ጂም ኢንሆፍና የኢትዮጵያ መንግሥት ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸው ተገለጸ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የመሥሪያ ቤታቸውን ሳምንታዊ ክንውን አስመልክተው ዛሬ መግለጫ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ የአሜሪካው ሴናተር ጂም ኢንሆፍ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ ጋር ውጤታማ የሚባል ውይይት ማድረጋቸውን እንዲሁም የተለያዩ ሀገራት የቀይ ባህር አካባቢን ለመቆጣጠር ፍላጎት ማሳየታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ፓሊሲ ከሁሉም ጋር ግንኙነት ማድረግን አንጂ ፊትን ወደ አንድ አቅጣጫ ማዞር እንዳልሆነ በመግለጫቸው የጠቀሱት አምባሳደር ዲና፣ አሜሪካዊው ሴናተር ኢትዮጵያን በተመለከተ ግልጽ አቋም ያላቸው፣ የሀገራቱን ግንኙነት ማሻከር እንደማይገባ የሚያምኑ መሆናቸውንና በሴኔቱ ስብሰባ ላይ ያንጸባረቁት አቋምም ይህንኑ የሚያረጋግጥ እንደሆነ ተናግረዋል።

“ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ ማዞር የቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ማሳያና ወቅቱን የማይመጥን ነው። መንግሥት አሁን ባለው ግምገማም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ወደ አንድ አቅጣጫ ለማዞር የሚያስገድደው ምንም አይነት ሁኔታ የለም” ያሉት ቃል አቀባዩ፣ ኢትዮጵያ ከሞሮኮ፣ ከስዊድን፣ ከኮትዲቯር፣ ቤላሩስ፣ ከጆርዳን እና ከሌሎች አገራት ጋር አዲስና የጋራ ጥቅሞችን ማዕከል ያደረጉ ጥብቅ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች መመስረቷን አስታውቀዋል።

በዚሁ ሳምንታዊ መግለጫቸው፣ የተለያዩ ሀገራት የቀይ ባህር አካባቢን ለመቆጣጠር ፍላጎት ማሳየታቸውን የገለጹት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ቀድሞ ከነበሩ ሀገራት ባለፈ ተጨማሪ ሀገራት በቀይ ባህር አካባቢ ወታደራዊ የጦር ማዕከል ለመመስረት እና አካባቢውን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ እንደሚገኙ አመልክተው “ቀድሞ በአካባቢው የጦር ቤዝ ከመሰረቱ ባለፈ የገንዘብ እና የመሳሪያ አቅማቸው እየፈረጠሙ የመጡ ሌሎች ሀገራት ጭምር በቦታው ትኩረት አድርገዋል። ይህ ፍላጎት ደግሞ በቀይ ባህር ዙሪያ በርካታ ተስተናጋጆች እንዲኖሩ ስለሚያደርግ አስቸጋሪ ሁኔታ ይፈጥራል” ብለዋል።

“አሁን ላይ የቀር ባህር ፖለቲካ እየተቀየረ ነው፤ ሀገራት ጡንቻ ማውጣት ሲጀምሩ በአካባቢው ችግር ለመፍጠር ይሞክራሉ” ሲሉ አያይዘው የገለጹት አምባሳደሩ፣ ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በቀጣይ 100 አነስተኛና መካከለኛ ግድብ እንገነባለን ማለታቸውን ተከትሎ ግብጽና ሱዳን ጉዳዩን እያራገቡት ስለመሆኑ ጠቅሰው “ህጉን አክብረን እስከሄድን ድረስ አንድ የሉአላዊ ሀገር መሪ 100 ግድብ እንገነባለን ቢል ምንድነው ችግሩ ሲሉ?” ጠይቀዋል።

“የዓለም አቀፍ ህግጋትን እስካከበርን ድረስ አይደለም 100 ይቅርና 1000 ግድቦችንም ብንገነባ በሌሎች ሀገራት ላይ ችግር አይፈጥርም። በህዳሴው ግድብ ጉዳይ ከታችኞቹ የተፋሰስ ሀገራት ጋር የሚደረገው ውይይትና የዲፕሎማሲ ጥረት እንደቀጠለ ነው። ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብቶቿ መጠቀሟም ሀገራቱ ላይ ጉዳት አያስከትልም” በማለት ተናግረዋል።

LEAVE A REPLY