ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው ‘ሲኤምሲ’ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ “ዶላር እናባዛለን” በማለት የአካባቢውን ህብረተሰብ ሲያጭበረብሩ የነበሩ ካሜሮናዊና ኢትዮጵያዊት፣ በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ኢንተለጀንስ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል፡፡
ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር በዋሉበት ሰዓት ዶላር እናባዛለን በማለት ለማጭበርበሪያ የሚጠቀሙባቸው ሁለት ካርቶን የጠቆረ ዶላር መሳይ ወረቀትና ሁለት ጠርሙስ ኬሚካል ይዘው መገኘታቸው ያስታወቀው ፖሊስ፣ ከማህበረሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ኢንተለጀንስ ሁለቱንም ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋሉንና በአሁኑ ሰዓት በተጠርጣሪዎቹ ላይ ምርመራው እየተጣራ እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡
እንደነዚህ አይነት ህገ-ወጥ ተግባር በሚፈጽሙ ግለሰቦች ዙሪያ ጥቆማ በመስጠት ህብረተሰቡ እያደረገ ያለውን ድጋፍና ትብብር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ፖሊስ አሳስቧል፡፡