ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ እና የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም፣ በትግራይ ክልል ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ በኢትዮጵያ ለሚንቀሳቀሱ የውጭ መገናኛ ብዙሀን ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፣ ለሕወሓት ቡድን የጦር መሳሪያ የማቅረብ ስራ የሚሰሩ በሰብዓዊነት ስም የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች በመንግስት እንደተደረሰባቸው ተጠቁሟል።
“በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የፍተሻ ጣቢያዎችን አዘጋጅቶ የቁጥጥር ስራ በመስራት ላይ ይገኛል” ያሉት የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት፣ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የሚመለከተው አካል በቀጣይ ቀናት ሰፊ ማብራሪያ እንደሚሰጥበትም ተናግረዋል፡፡
መንግስት ከወራት በፊት በሰጠው ፈቃድ መሰረት እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች በትግራይ ክልል ያለገደብ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ የገለጹት ቢልለኔ ስዩም፣ ይሁን እንጂ የደህንነት ችግር አለባቸው ተብለው በተለዩ ቦታዎች ላይ የመከላከያ ሠራዊት እገዛ እንደሚያስፈልግና የጸጥታ ችግር ባለባቸው ቦታዎች ላይ መድረስም ፈታኝ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የመንግስት ጦር የሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይደርስ በመከልከል ላይ እንደሚገኝ የሚነገረው ወሬ ሀሰት መሆኑን፣ ለአብነትም ገበሬዎች የእርሻ ስራዎቻቸውን እንዳያከናውኑ ስለመከልከላቸው በስፋት የተሰራጨው መረጃ ለፖለቲካ ፍጆታ የሚውል የሀሰት ወሬ ስለመሆኑ፣ ይህም ሆን ተብሎ በሕወሓት አካላት የሚነዛ ወሬና ዓላማውም የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ እና የሚዲያ አውታሮችን ቀልብ በመሳብ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር እንደሆነና የጠቀሱት ፕሬስ ሴክሬታሪያቷ ቢልለኔ “ስታስቡት ለምን ብሎ ነው መከላከያ ለ30 ዓመታት ያህል አብሮት በኖረው እና በአምበጣ ወረርሽኝ ወቅት አብሮት ሲለፋ በነበረው ገበሬ ላይ እንዲህ አይነት በደል የሚፈጽመው?” በማለትም ጠይቀዋል፡፡
በተጨማሪም፣ የመከላከያ ሚኒሰቴርን ሪፖርት በመጥቀስ የኤርትራን ጦር ከኢትዮጵያ የማስወጣት ሂደት መጀመሩንና በሁለቱ ሀገራት በተደረሰው ስምምነት መሰረት የመውጣቱ ሂደት የሚቀጥል መሆኑንም ፕሬስ ሴክሬታሪያቷ አስታውቀዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያቷ ቢልለኔ ስዩም ጋር በመሆኑ የትግራይ ክልልን ወቅታዊ ሁኔታ በሚመለከት በኢትዮጵያ ለሚንቀሳቀሱ የውጭ መገናኛ ብዙሀን ማብራሪያ የሰጡት የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በበኩላቸው፣ ከጦርነቱ ዝግጅት ጀምሮ “በሕወሓት የተፈጸሙ” ያሏቸውን የወንጀል ድርጊቶች፣ እንዲሁም በጦርነቱ ወቅት በተዋጊ ኃይሎች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል።