ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ኢትዮጵያ ይሄን የመሰለ መልከአምድር ይዛ፣ ውሃ ይዛ መንግስት እና ህዝብ በተለይም አርሶአደሩ በትክክል የግብርናን ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ ጉዳይ ከሃገር ህልውና ጉዳይ ጋር የተያያዘ መሆኑን ኣውቆ ሰርተን እራሳችንን መመገብ ካልቻልን ስንዴ እየለመንን ነጻነት የሚባል ነገር የለም። ስንዴ እየለመንን የሃገር ክብር የሚባል ነገር የለም፣ ስንዴን ከመለመን ነጻ መውጣት የሚያስችል ብቁ የሆነ መልከአምድር አለን” ሲሉ ዛሬ በጽ/ቤታቸው የማህበራዊ ትስስር ገጽ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በሌላም በኩል፣ የኦሮሚያ ልማት ማኅበር ዓመታዊ የማጠቃለያ መድረኩን “አንድነት ለልማት” በሚል መሪ ቃል በአንድነት ፓርክ ዛሬ ባካሄደበት ወቅት በመድረኩ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ኢትዮጵያን ለማሻገር በሕብረት መቆም አለብን፤ ከአበርን ኢትዮጵያን የአፍሪካ ተምሳሌት ማድረጋችን አይቀርም” ብለዋል።
በዚሁ ፕሮግራም ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንም ኢትዮጵያን ጠንካራ እና ተጽኖ ፈጣሪ ለማድረግ በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።