ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በቅርቡ በተቋቋመው “የአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ወረዳ ፍርድ ቤት ሥልጣን እና ተግባራት ላይ ማብራሪያ ይሰጠኝ” ሲል የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን በደብዳቤ ጠይቋል፡፡
ኢዜማ ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በላከው ደብዳቤ፣ በተለያዩ መንግሥታዊና የግል ሚዲያዎች “የፊንፊኔ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት በይፋ ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት ጀመረ” በማለት የተሰሩት ዘገባዎች፣ በሕገ መንግሥቱ ለአዲስ አበባ ከተማ የተሰጠውን ራስን በራስ የማስተዳደር ሥልጣን የሚጋፋ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብሏል፡፡
የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (ኦቢኤን) የአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ኩመላ ቡላን ጠቅሶ በሰራው ዘገባ “…በፊንፊኔ ከተማ የሚኖሩ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆችም ሕገ መንግሥታዊ መብታችውን በመጠቀም በዚህ ፍርድ ቤት በቋንቋቸው የመዳኘትና ተደራሽ የሆነ የፍትህ አገልግሎት የማግኘት መብትም ያገኛሉ ብለዋል” በማለት መዘገቡን ያስታወሰው ኢዜማ፣ ይህንን ዘገባ ተከትሎ አዲስ በተከፈተው ፍርድ ቤት ሥልጣንና ተግባራት ላይ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ማብራሪያ ጠይቋል፡፡
“የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 49 (2 እና 3) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን እንዳለው፣ ተጠሪነቱም ለፌደራል መንግሥት አንደሆነ በግልጽ ደንግጓል” ያለው ኢዜማ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራሱን በራሱ ያስተዳድራል ሲባል ከተማው የራሱ ሕግ አውጭ፣ ሕግ አስፈጻሚ እና ሕግ ተርጓሚ ይኖረዋል ማለት መሆኑን ጠቁሞ “ተጠሪነቱ ለፌደራል መንግሥት ነው ማለት ደግሞ በአዲስ አበባ ጉዳዮች ላይ የመጨረሻ የመወሰን ሥልጣን ያለው አካል የፌደራል መንግሥቱ ብቻ ነው ማለት ነው” ሲል አመላክቷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን ለሚገጥማቸው ማናቸውም ጉዳይ፣ የትኛውም ብሔር ጀርባ ቢኖራቸውም የመዳኘት ሥልጣኑ የከተማ መስተዳደሩ ፍርድ ቤቶችና የፌደራል ፍርድ ቤቶች መሆኑን የጠቀሰው ኢዜማ “አንድ ክልል የዚህ ብሔር ተወላጆችን ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ ከተማ ቢሆንም የመዳኘት ሥልጣን ይኖረኛል ማለቱ በሕገ መንግሥቱ ለፌደራል መንግሥቱ የተሰጠውን ሥልጣን የሚጋፋ፤ በአዲስ አበባ ቻርተር አዋጅ ቁጥር 87/1989 እንዲሁም እሱን ያሻሻለው አዋጅ ቁጥር 361/1995 የአዲስ አበባ አስተዳደር ራስ ገዝ ከመሆኑም ባሻገር በፌደራሉ መንግሥት የዳኝነት ፈቃደ ሥልጣን ሥር በማይወድቁ ጉዳዮች ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች አና የቀበሌ ማኅበራዊ ፍርድ ቤቶች ብቻ ሥልጣን እንደሚኖራቸው ተብሎ የተደነገገውን በግልጽ የሚቃረን ሆኖ አግኝቼዋለሁ” ብሏል፡፡
አሁን ለተቋቋመው ፍርድ ቤት የሕግ መሰረት ተደርጎ የተጠቀሰው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፍርድ ቤቶች አደረጃጀት ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር 216/2011 በአንቀጽ 24 ላይ ከተዘረዘሩት የኦሮሚያ ፍርድ ቤቶች የተሰጣቸው ሥልጣን እና ተግባራት ላይ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችን ጉዳይ የማየት ሥልጣን እንዳላቸው ባልጠቀሰበት ሁኔታ፣ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችን ጉዳይ የማየት የዳኝነት ፈቃደ ሥልጣን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፍርድ ቤቶች አላቸው ተብሎ መገለጹ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ እና ምንም ዓይነት የሕግ መሰረት የሌለው ነው ያለው ኢዜማ፣ በአንድ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች የብሔር ማንነታቸው ላይ በመመስረት የተለያየ የዳኝነት መብት ይኖራቸዋል ብሎ ፍርድ ቤት መክፈት የዜጎቸን በሕግ ፊት በእኩልነት የመታየት ሰብአዊና ሕገ መንግሥታዊ መብትን የሚጥስ ከመሆኑም ባለፈ የዜጎችን ተከባብሮ የመኖር እሴት የሚሸረሽር ነው የሚል እምነት እንዳለው ኢዜማ በደብዳቤው ገልጿል፡፡
በአንድ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች የብሔር ማንነታቸው ላይ በመመስረት የተለያየ የዳኝነት መብት ይኖራቸዋል ብሎ ፍርድ ቤት መክፈት የዜጎችን በሕግ ፊት በእኩልነት የመታየት ሰብዓዊና ሕገ መንግሥታዊ መብትን የሚጥስ ተግባር መሆኑን የጠቀሰው ኢዜማ፣ ይህ ዓይነቱ ድርጊት የዜጎችን ተከባብሮ የመኖር ዕሴት ይሸረሽራል ብሎ እንደሚያምንም ገልጿል፡፡
“ጠቅላይ አቃቤ፣ ይህንን ከሕገ መንግሥት ማዕቀፍ ውጪ የሆነ ኢ-ሕገ መንግስታዊ ተግባር እንዲያስቆም” ሲልም ፓርቲው ለጠቅላይ አቃቤ ሕግ በላከው ደብዳቤ ማብራሪያ እንዲሰጠው ጥያቄውን አቅርቧል፡፡