የደህንነት እና የፖሊስ መርማሪ ነኝ እያለ ሲያጭበረብር የነበረው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ!

የደህንነት እና የፖሊስ መርማሪ ነኝ እያለ ሲያጭበረብር የነበረው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜናስንታየሁ ቢርጉ ካየና፣ ስንታየሁ ተመስጌን አበራና ስንታየሁ ደምሴ የተባሉ ስሞችን፣ እንዲሁም የተለያዩ የስራ ድርሻና አድራሻ ያላቸው ሐሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀምና በማጭበርበር ወንጀል የተጠረጠረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የፋይናንስና ንግድ ነክ ወንጀል ምርመራ ዳይሬክቶሬት የህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀል ምርመራ ኃላፊ አቶ ሽመልስ ጥበቡ እንደገለጹት፣ ሀሰተኛ ስምና ሰነዶችን እየተጠቀመ የማጭበርበር ተግባር ሲፈፅም የቆየው ግለሰቡ “ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት፣ ማታለልና በባለስልጣን ስም መነገድ” የሚሉት ከተጠረጠረባቸው ወንጀሎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

በአንደኛው ሀሰተኛ መታወቂያው ላይ የፕሮቪዥን ኃላፊ እንደሆነ፣ በሌላኛውም የስራ ድርሻው መርማሪ መሆኑን የሚገልጽ ሐሰተኛ መታወቂያ አስወጥቶ ሲገለገል መቆየቱንና ፖሊስ ባደረገው ምርመራ እንደደረሰበት የተናገሩት አቶ ሽመልስ ጥበቡ፣ ግለሰቡ በወንጀል ተጠርጣሪዎች ላይ ብርበራ ሲደረግ እንደ ጠቋሚና ተባባሪ ሆኖ በመቅረብ የከፍተኛ መንግስት ባለስልጣናትን ስም እየጠራ ጉቦ ይቀበል እንደነበርም አመልክተዋል።

ግለሰቡ ሚያዝያ 19 ቀን 2013 ዓ.ም ወደተክለብርሐን አምባዬ ኮንስትራክሽን ድርጅት በመሄድ “ድርጅታችሁ ሊታገድና ሊዘጋ ነው” በሚል ማስፈራሪያ 500 ሺህ ብር ጉቦ መቀበሉንና በህገ-ወጥ መንገድ የተገኘውን ገንዘብም ለማሸሽም ወደባለቤቱ የሂሳብ ደብተር ሲያስተላልፍ እንደነበር ፖሊስ በማስረጃ ማረጋገጥ መቻሉን የተናገሩት አቶ ሽመልስ፣ ከቴሌ ኮሙዩኒኬሽንም የእሱ ባልሆነና ስንታየሁ ደምሴ በሚል ስም የሐሰተኛ መታወቂያ ሲም ካርድ እያወጣ ሲጠቀም መቆየቱንና ግለሰቡ ሲጠቀምባቸው የነበሩት መታወቂያዎች ሁሉ ሐሰተኛ መሆናቸውን ፖሊስ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመሆን ባደረገው ምርመራ እንዳረጋገጠም ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ኢንተለጀንስ፣ በግለሰቡ ላይ ባደረገው ክትትል ግለሰቡን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በቁጥጥር ስር እንዳዋለውና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮም የክስ መዝገቡን ለሚመለከተው አቃቤ ህግ መላኩን ኃላፊው አያይዘው ተናግረዋል፡፡

LEAVE A REPLY