ጠ/ሚ/ር ዐቢይ “ልበ ብርሃን ባለፀጋ” ሲሉ አወደሱ!
ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የታዋቂው ባለሐብት አቶ ወርቁ አይተነው ንብረት የሆነውና ከ5 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት “ደብሊው ኤ ኢንዱስትሪያል የምግብ ዘይት ኮምፕሌክስ” ዛሬ በደብረ ማርቆስ ከተማ ተመርቋል፡፡
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን እና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ በሥነ ሥርዓት ላይ “መሥራትን ብቻ ሳይሆን ያለንን ማካፈልንም ተምረናል” በማለት በተለይም ፋብሪካው የተገነባበትን ቦታ በፈቃደኝነት ለለቀቁ አርሶ አደሮች የተደረገው ሽልማት የባለሐብቱን ማንነት እና አርቆ አሳቢነት የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰው ባለሃብቱንም “ልበ ብርሃን ባለፀጋ” ሲሉ አወድሰዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዚሁ የፋብሪካው ምረቃ ላይ ባደረጉት ንግግር “ኢትዮጵያ ትናንትን አሳልፋ ዛሬ ላይ ለመድረስ እና ነገን ለማለም ፈጣሪዋ፣ በክፉ ጊዜ ህይዎቱን በሰላም ጊዜ ደግሞ ጉልበቱን የማይሰስት ሕዝቧ እና ተፈጥሮ ያለልክ የቸረቻት ፀጋዎቿ ምሰሶዎቿ ናቸው። በፈጣሪ ታምነን እና አንድነታችን ጠብቀን ፀጋዎቻችንን ማልማት ከቻልን የኢትዮጵያን ትንሳኤ ማስቆም የሚችል ኃይል አይኖርም። …ጎጃም ደብረ ማርቆስ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና ክብር የማይደራደሩት የዘለቀ ላቀው እና የበላይ ዘለቀ ሀገር ናት። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጀግንነት በየዘመናቱ የሚገለጥበት መስክ አለው። ብዙ ጦር አሰልፎ እና መሣሪያ አንግቶ ጫካ መግባት እና መሸፈት ያ ዘመን የሚጠይቀው ጀግንነት ነበር። አሁን ግን እንደ ልበ ብርሃኑ ባለፀጋ አቶ ወርቁ አይተነው ግዙፍ ፋብሪካ ገንብቶ የሥራ ዕድል መፍጠርን የሚያክል ጀግንነት የለም። ሁላችንም ይህንን ወቅቱ የሚጠይቀውን ጀግንነት ልንላበስ ይገባል” ብለዋል፡፡
አያይዘውም፣ አገር ለማፍረስ ከዳር ሆነው የሚተጉ የውጭ ኃይሎች እንዳሉ በመጥቀስ “ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን አስጠብቀው በጋራ እስከዘለቁ ድረስ ኢትዮጵያ ፈርሳ አታውቅምና ዛሬም አትፈርስም” ሲሉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ነፃ ሀገር ስለተረከብን ነፃ ሀገር እናስረክባለን፤ ድሃ ሀገር ብንረከብም የበለፀገች ኢትዮጵያን እናስረክባለን። ዛሬ የታየውን ልግስና እና መከባበር፣ ፍቅር እና አንድነት እንደ ጉልበት ተጠቅመን ከኢትዮጵያ አልፎ ጎረቤት ሀገራትን የሚሸልም ባለሃብት ለመፍጠር አልመን ልንሠራበት ይገባል” በማለትም አሳስበዋል፡፡
በደብረ ማርቆስ ከተማ የተገነባው “የደብሊው ኤ/WA ኢንደስትሪያል የምግብ ዘይት ኮምፕሌክስ የዛሬው ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው “ደብሊው ኤ የዘይት ፋብሪካ የጽናትና የታታሪነት ምሳሌ ነው። ምንም እንኳን ፋብሪካው በርካታ እንቅፋቶች ቢገጥሙትም ፈተናዎችን አልፎ ለስኬት መብቃት እንደሚቻል ሌሎች ባለሃብቶች ከደብሊው ኤ ፋብሪካ መማር ይችላሉ” ብለዋል።
ደብሊው ኤ ኢንዱስትሪያል የምግብ ዘይት ኮምፕሌክስ፣ ኢትዮጵያ በለውጡ ማግስት ያስቀመጠችውን ወሳኝ የኢንዱስትሪ ልማት አቅጣጫ በግልጽ የሚያሳይ እንደኾነ ያመለከቱት አቶ አገኘሁ፣ በተለይ የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚና የኢንዱስትሪ ትስስርን በግልጽ የሚያሳይ መኾኑን ጠቅሰው አቶ ወርቁ አይተነውን ጨምሮ ሌሎች ባለሀብቶችም በዘርፉ መሰማራታቸው የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ምርታቸውን ተደራድረው እንዲሸጡ ያደርጋል፤ ምርታቸውን ለማሳደግም ይረዳል። ደብረ ማርቆስ ባለፉት ዓመታት በተሰጣት ዝቅተኛ ትኩረት ልማቷ ዝቅተኛ ነበር። ነገር ግን ባለፉት ሦስት ዓመታት በተሠራው ሥራ ከተማዋን ምቹ፣ ለኢንቨስትመንት ሳቢ፣ ማራኪና ተመራጭ ማድረግ ተችሏል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የፌዴራል ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበልም “በቅርቡ ወደ ሥራ እየገቡ ያሉ ፋብሪካዎች ኢትዮጵያ የመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በሀገር ውስጥ የማምረት እቅዷን ስኬታማነት የሚያሳዩ ናቸው። በኢትዮጵያ በአሁን ጊዜ የቅባት እህሎችን ጨምቀው የሚያጣሩ 25 መካከለኛና መለስተኛ ኢንዱስትሪዎች ከአጠቃላይ ከምግብ ዘይት ፍላጎት አንፃር 6 ነጥብ 2 በመቶ ብቻ ይሸፍናሉ፡፡ በቅርቡ የፓልም የምግብ ዘይት ድፍድፍን በማጣራት ምርታቸውን ወደ ገበያ እያስገቡ የሚገኙ 5 ፋብሪካዎች የዘይት ፍላጎት 40 ነጥብ 2 በመቶ መሸፈን ችለዋል። ደብሊው ኤ የምግብ ዘይት ኮምፕሌክስ ፋብሪካን ሳይጨምር 30ዎቹ ፋብሪካዎች በድምሩ የፍላጎቱን 46 ነጥብ 7 መሸፈን ችለዋል። ዛሬ የተመረቀው ደብሊው ኤ የምግብ ዘይት ኮምፕሌክስ ፋብሪካ የግብዓት እጥረት ካልገጠመው በስተቀር በቀን 18 ሺህ ኩንታል ጥሬ እቃ በመጠቀም የምግብ ዘይት ፍላጎቱን በእጅጉ ያሻሽላል ተብሎ ይጠበቃል። የምግብ ዘይት ኮምፕሌክስ ፋብሪካዎች የፍጆታ እቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ ስለሚያቀርቡ የኑሮ ውድነቱን በማቃለል ጠቀሜታ ይኖራቸዋል” በማለት በዚሁ የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር አስታውቀዋል።
በባለሀብቱ አቶ ወርቁ አይተነው ደብረ ማርቆስ ከተማ ላይ፣ ከ5 ነጥብ ሁለት ቢሊየን ብር በላይ የሆነ ወጪ ተደርጎበት፣ በሊዝ በተገኘ 101 ሺህ 103 ካ.ሜ ቦታ የተገነባው ግዙፉ “WA ዘይት ፋብሪካ የሰሊጥ፣ የአኩሪ አተር፣ የኑግ፣ የሱፍ እና የለውዝ የምግብ ዘይቶችን በዋናነት የሚያመርት ሲሆን ድፍድፍ የፓልም ዘይትንም የሚያጣራ ሲሆን፣ ባለ 1፣ ባለ 3፣ ባለ 5፣ ባለ 10 እና ባለ 20 ሊትር ዘይቶችን አምርቶና አሽጎ ለገበያ እንደሚያቀርብ፣ ከምርት በኋላ የሚገኘው ተረፈ ምርትም የእንስሳት መኖ ሆኖ ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ ዝግጅት መጠናቀቁ፣ በአሁኑ ጊዜም ከ1500 በላይ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍል ቀጥተኛ የሆነ የሥራ መፍጠሩና ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምርም ከ3000 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራል ተብሎ እንደሚታመን ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።