ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ከአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ ከተማ ተከስቶ በነበረው ረብሻና ግርግር “ራሳችሁን አዘጋጁ በሚል የአዲስ አበባ ወጣቶችን ለአመጽ እንዲነሳሱ ቀስቅሰሀል” በሚልና በሌሎች ተያያዥ ወንጀሎች ተጠርጥሮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለውና ላለፉት 11 ወራት በማረሚያ ቤት እስር ላይ የሚገኘው የባልደራስ ፓርቲ ሊቀመንበሩ እስክንድር ነጋ አዲስ መጽሐፍ ተመረቀ።
ፖለቲከኛው እስክንድር ነጋ፣ በቃሊቲ ወህኒ ቤት የእስር ቆይታው በተለያዩ ጊዜያት በልዩ ልዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር፣ የፃፋቸው ፅሁፎች ስብስብ የሆነውና “ድል ለዴሞክራሲ” በሚል ርዕስ በአንድ ጥራዝ ተሰናድቶ በቅርቡ ለንባብ የበቃው አዲሱ መጽሐፍ፣ በአዲስ አበባ ራስ አምባ ሆቴል ዛሬ ከ11:00 ሰዓት ጀምሮ በተከናወነ ዝግጅት የተመረቀ ሲሆን፣ በመጽሐፉ ላይ ዳሰሳ ያቀረቡት ጋዜጠኛ ሰለሞን ሹምዬ፣ አርቲስት አስቴር በዳኔና የዓባይ ሚዲያ ፕሮግራም አዘጋጇ መአዛ መሐመድም በእስክንድር ስራዎችና የግል ስብዕና ላይ በማተኮር ሰፋ ያሉ ትንተናዎችን አቅርበዋል።
በተለይም አርቲስት አስቴር በዳኔ የእስክንድርን ጠንካራና ደካማ ጎኖች በዳሰሰችበት ምልከታዋ የፕሮግራሙን ታዳሚዎች በብዙ ያስገረመች ሲሆን፣ በዚሁ ዳሰሳዋም “እስክንድር ከሰብዓዊ መብት ተሟጋችነትና ከጋዜጠኛነት አልፎ ራሱን ወደ ፖለቲከኛነት ሲያሻግር በርካታ የፖለቲካ ሰዎችን ጨምሮ ብዙዎች ተችተውት ነበር። በሚያነሳቸው ሀሳቦችና የፖለቲካ አጀንዳዎችም እብድ እስከማለት ደርሰው ነበር። እነዚያ እብድ ነው ያሉት ግን ዛሬ የእሱን እውነት ይዘው አደባባይ ወጥተዋል። እብድ ያሉበትን አጀንዳ ለምረጡኝ ቅስቀሳቸው እየተጠቀሙበት ይገኛሉ” ብላለች።
በክብር እንግድነት ተጋብዞ በፕሮግራሙ የተገኘው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በበኩሉ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ “በኋለኛው ዘመን ኢየሱስን መስለው ከሚመጡ ሀሳበ መሲሆች ተጠበቁ” የሚለውን አስተምህሮ ጠቅሶ “የዘመኔ ሰዎችም ዴሞክራሲ ዴሞክራሲ ከሚሉ አታላዮች ራሳችሁን ጠብቁ፤ እንዳትታለሉ” ሲል ምክረ ሃሳብ አንስቷል።
በመጨረሻም፣ በባልደራስ ፓርቲ የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገለታው ዘለቀ በኩል ለመጽሐፉ እውን መሆን የየራሳቸውን ድርሻ ላበረከቱ ግለሰቦችና ተቋማት የምስጋና ምስክር ወረቀት ተሰጥቶ የፕሮግራሙ ፍጻሜ ሆኗል።