ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ ንብረትነታቸው የሕወሃት የሽብር ቡድን አባላት የሆኑ በኪራይ፣ በውክልና በሌሎች መንገዶች ተይዘው የሚገኙ ሀብቶች ላይ ጥቆማ እንዲቀርብ ጥሪ አቀረበ፡፡
በራሳቸው በቤተሰቦቻቸውና በቅርብ ሰዎች ስም የያዙት በአዲስ አበባና በሌሎች የክልል ከተሞች የሚገኝ የሕወሃት የሽብር ቡድን አባላት ንብረት ላይ ማቅረብ እንደሚቻል ያመለከተው ፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ የህወሃት የሽብር ቡድን በመከላከያ ሠራዊታችን የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከፈጸመበት ማግስት ጀምሮ በጥፋት ቡድኑና አባላቱ ላይ የወንጀልና የሃብት ምርመራዎች ሲያከናውን የነበረ መሆኑ አስታውሶ “በወንጀል የተገኘና በአገር ውስጥ ወይም በውጭ አገር የተደበቀ ሀብት ላይ ጥቆማ እንዲቀርብ ባቀረብነው ጥሪ መሰረት ከሕዝብ የተሰጡ ብዛት ያላቸው ጥቆማዎችና መረጃዎችን መሰረት በማድረግ የአሸባሪ ድርጅቱንና አባላትን ሃብት ጨምሮ በተደረገው የማጣራት ሥራ በርካታ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ ለዚህም ተቋማችን ለሕዝቡ ከፍተኛ ምስጋና ያቀርባል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሕወሃት የሽብር ቡድን አባላት ፣ በቤተሰቦቻቸዉና በቅርብ ሰዎች ስም በአዲስ አበባና በሌሎች የክልል ከተሞች ያሉ የማይንቀሳቀሱና ተንቀሳቃሽ ቋሚ ንብረቶችን በአካል በመለዬት የጥፋት ቡድኑ ንብረቶችንና ከንብረቶቹ የሚገኘውን ገቢ ለሽብርና ሌሎች ወንጀሎች መጠቀም እንዳይችል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ሰፊ የመከላከል ሥራ እየተሰራ ይገኛል፡፡
የሕወሃት የሽብር ቡድን አባላት የሆኑ ንብረቶችን በኪራይ፣ በዉክልና፣ በአደራ፣ በጠባቂነት ወይም በሌላ ማንኛዉም መንገድ ይዛችሁ የምትገኙ ሰዎች ይህ ማስታወቂያ ከተነገረበት ጊዜ ጀምሮ በ 7 (ሰባት) ተከታታይ የሥራ ቀናት ውስጥ ለፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሪፖርት እንድታቀርቡ፣ የሕወሃት የሽብር ቡድን አባላት፣ በራሳቸው፣ በቤተሰቦቻቸውና በቅርብ ሰዎች ስም የያዙት በአዲስ አበባና በሌሎች የክልል ከተሞች የሚገኝ ንብረት አስመልክቶ ከሕዝቡ ተጨማሪ ጥቆማዎች በአካል፣ በስልክና በኢሜል እንዲቀርብ እየጠየቅን በአካል መቅረብ ለማይችሉ ጥቆማ አቅራቢዎች በሚከተሉት የስልክና ኢሜል አማራጮች ማቅረብ ትችላላችሁ፡-
ሰልክ ፡- +251112733154
Email: – assetrecovery@eag.gov.et
የሪፖርትና ጥቆማ ማቅረቢያ ቦታ ልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ በሚገኘው የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሕንጻ 1ኛ ፎቅ በወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመለስ ዳይሬክቶሬት ጄነራል ነው” ሲል አስታውቋል።