ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ (ባልደራስ) ፓርቲ፣ ለፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደርና ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ፍ/ብሔር ችሎት ባስገባቸው ሁለት ደብዳቤዎች፣ በእስር ላይ የሚገኙት የፓርቲው እጬ የምርጫ ተወዳዳሪዎች ደህንነት እንዳሳሰበው ገልፆ፣ ያለመከሰስ መብታቸው ተጠብቆ ከእስር እንዲለቀቁ ጠይቋል።
ፓርቲው ሰኔ 2 ቀን 2013 ዓ.ም ለፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ባስገባው ደብዳቤ “የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ አመራር የሆኑትና የ2013 ዓ.ም የአዲስ አበባ ም/ቤት እጩ ተወዳዳሪ የሆኑት አቶ እስክንድር ነጋ በማረሚያ ቤታችሁ የሚገኙ መሆኑ ይታወቃል፡፡ እኚህ የፓርቲያችን መሪ በቅርቡ በከፍተኛ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት እጩ ሆነው ለ2013 ዓ.ም ምርጫ መወዳደር እንዲችሉ የተወሰነላቸው እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ እጩ ተወዳዳሪ አቶ እስክንድር ነጋ በአሁኑ ሰዓት በእስር ቤቱ ውስጥ ለህይወታቸው፣ ለስነ ልቡናቸውና ለጤናቸው ከፍተኛ አደጋ ላይ መሆናቸውን በተደጋጋሚ ገልፀዋል፡፡ ማረሚያ ቤቱ እኚህ ሰው የህዝብ ተመራጭ እጩ መሆናቸውንና የፖለቲካ ከፍተኛ መሪ መሆናቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለደህንነታቸው አስጊ ባልሆነ ቦታ እንዲያቆያቸው እየጠየቅን በእኚህ መሪ ላይ ማንኛውም አካላዊም ሆነ ስነ ልቦናዊ ጉዳት ቢደርስ ከማረሚያ ቤቱ አያያዝ ችግር የመጣ በመሆኑ የማረሚያቤ ቱ አስተዳደር በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጠየቅ ማሳወቅ እንወዳለን” ብሏል።
“ከዚሁ ጋር በተያያዘ እጩ ተወዳዳሪ ወ/ሮ ቀለብ ስዩም እንደዚሁ ከፍተኛ የደህንነት ስጋት እንዳለባቸው እየገለፁ በመሆኑ ለሁለቱም እጩ ተወዳዳሪዎች በጣም አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጥ በጥብቅ እንጠይቃለን” ሲልም አመልክቷል።
እንደዚሁ ሁሉ፣ ፓርቲው ሰኔ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ፍ/ብሔር ችሎት “እነ እስክንድር ነጋ ያለመከሰስ መብታቸው ተጠብቆ ከእስር እንዲለቀቁ” ሲል ባቀረበው አቤቱታ “የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች እና ዕጩዎች ፕሬዝዳንት አቶ እስክንድር ነጋ ፣ አስቴር ስዩም ፣ስንታየሁ ቸኮል እና አስካለ ደምሌ በዓቃቤ ሕግ በግፍ ታስረው የነበረ ቢሆንም፣ በ6ኛው ምርጫ እጩ ሆነው በባልደራስ መቅረባቸው ይታወቃል። በዚሁ መሠረት እጩ ሆኖ የቀረበ ሰው እጅ ከፍንጅ በከባድ ወንጀል እስካልተያዘ በስተቀር ያለመከሰስ መብት አለው” ሲል አመልክቷል።
በተያያዘ፣ የእነ እስክንድር ነጋ ጠበቆች ያለመከሰስ መብታቸው ተጠብቆ ክሱ ተቋርጦ ከእስር እንዲለቀቁ ለፍ/ቤቱ ያቀረቡት አቤቱታ ላይ ዐቃቤ ሕግ መልስ እንዲሰጥበት ለዓርብ ሰኔ 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ እንደተሰጠ የባልደራስ የሕግና የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ሄኖክ አክሊሉ ገልጸዋል።
“የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዘዳንት እና እጩ የሆነው እስክንድር ነጋ በአዲስ አበባ ቃሊቲ ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት በግፍ ታስሮ የሚገኝበት ሁኔታ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮብናል” በማለት መግለጫ የሰጠው ፓርቲው “የእስክንድር ነጋን አያያዝ ፓርቲው ሲከታተል የቆየ ሲሆን፣ በተለይም ከግንቦት 27 ቀን 2013 ዓ/ም ጀምሮ ቀድሞ ታስሮበት ከነበረው ‘ዋይታ’ ተብሎ ከሚጠራው ዞን በደረሰበት የሰብዓዊ በደል ምክንያት 8ኛ ዞን ተብሎ ወደሚጠራው ቦታ እንዲዛወር ተደርጓል፡፡ ሆኖም አሁን ታስሮ ባለበት ቦታ በእስረኞች የደህንነቱ ሁኔታ፣ አደጋ ላይ እንደወደቀ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ማረሚያ ቤቱ ድረስ በመሄድ ለማረጋገጥ ችለዋል…የቃሊቲ ማረሚያ ቤትም ሆነ በሕግ የእስረኞችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት የተጣለበት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ የእስክንድር ደህንነት አደጋ ላይ በመውደቁ ምክንያት ሊፈጠር ለሚችል ማናቸውም ነገር ሙሉ ለሙሉ ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ ማስገንዘብ እንወዳለን” ሲልም አስታውቋል።