“የለጋሽ አገራት የበጀት ድጋፍ በመቀነሱ” የተወካዮች ምክር ቤት 26 ቢሊዮን ብር በጀት...

“የለጋሽ አገራት የበጀት ድጋፍ በመቀነሱ” የተወካዮች ምክር ቤት 26 ቢሊዮን ብር በጀት አጸደቀ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜናለፌዴራል መንግሥት የ2013 በጀት ዓመት ተጨማሪ በጀትና የወጪ አሸፋፈን ማስተካከያን፣ በቀጥታ ወደ ቋሚ ኮሚቴው ሳይመራ ዝርዝር ውይይት ተደርጎበት ውሳኔ እንዲሰጠው ማድረግን ቀዳሚ አጀንዳው ያደረገውና ዛሬ የተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ስብሰባ፣ ከውጭ የሚገኘው የቀጥታ ድጋፍ በመቀነሱ ምክንያትና በሀገር ውስጥ መሸፈን በማስፈለጉ፣ የ26 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት አጽድቋል።

ከቀናት በፊት በ2013 በጀት ዓመት ሥራ ላይ እንዲውል ጠቅላላ ብር 476 ቢሊዮን ብር በጀት ባጸደቀው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዛሬ ስብሰባ፣ የተለያዩ ወጪዎችን ቀጥታ የበጀት ድጋፍ ለማድረግ እና በተገቢው መልኩ ለመሸፈን እንዲቻል በሚል ከመንግሥት ጎን ለመሆን ፈቃደኛ ከሆኑ የልማት አጋሮች ጋር የገንዘብ ድጋፍ ስምምነቶች መደረጋቸው ተነስቷል፡

በምክር ቤቱ ተገኝተው ስለጉዳዩ ዝርዝር ማብራሪያ የሰጡት የመንግሥት ተጠሪ ረዳት ሚኒስትር ጫኔ ሽመካ፣ በወቅቱ የነበረው የበጀቱ ዝግጅት የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎችን ተለዋዋጭነት ታሳቢ ያደረገ እንደነበር አውስተው “አሁን እንደ ሀገር ለገጠሙ የኢኮኖሚ ተግዳሮቶች መፍትሔ ለመስጠት በ2013 በጀት ላይ ለውጦችን ማድረግ የሚያስገድድ ሆኖ ተገኝቷል” በማለት የቀረበው የተጨማሪ በጀት ጥያቄና የወጪ አሸፋፈል ማስተካከያ ተግባራዊ እንዲሆን ለማስቻል በቀጥታ ጉዳዩ ለቋሚ ኮሚቴው ሳይመራ ለሕዝብ እንደራሴዎቹ ዝርዝር የውሳኔ ሀሳብ መቅረቡን አመልክተዋል፡፡

የተጨማሪ በጀቱን አስፈላጊነት በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የመንግስት ተጠሪ ረዳት ሚኒስትሩ፣ ከውጭ የሚገኘው የቀጥታ ድጋፍ በመቀነሱ ምክንያት በሀገር ውስጥ ቀጥታ ብድር መሸፈን ማስፈለጉን መነሻ በማድረግ “በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ሕግን ለማስከበር ከተወሰደው እርምጃ ጋር ተያይዞ የተከሰቱ ወጪዎች፣ በድርቅ ለተጎዱ፣ ለተፈናቀሉ እና ለተመላሾች የዕለት ዕርዳታ፣ ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል፣ ለማዳበሪያ ድጎማ፣ ለጎርፍ መከላከል፣ ለማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ለአቅም ግንባታ ፕሮጀክት እና የመጠባበቂያ በጀት በመጠናቀቁ በቀጣይ ወራቶች ለሚያስፈልጉ የተለያዩ ወጪዎች ለመጠባበቂያ በጀት መመደብ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል” ብለዋል፡፡

የተለያዩ ወጪዎችን ቀጥታ የበጀት ድጋፍ ለማድረግ እና በተገቢው መልኩ ለመሸፈን እንዲቻል በሚል ከመንግሥት ጎን ለመሆን ፈቃደኛ ከሆኑ የልማት አጋሮች ጋር የገንዘብ ድጋፍ ስምምነቶች መደረጋቸውም አያይዘው የገለጹት ረዳት ሚኒስትሩ፣ ከደቡብ ኮሪያ መንግሥት የቀጥታ ድጋፍ በብድር የተገኘ የ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር፣ የኮሮና ቫይረስ ቀውስ አስቸኳይ ምላሽ የበጀት ድጋፍ፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክ 5 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ለኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ምላሽ በጀት የድጋፍ ፕሮገራም እና ከጀርመን ተራድኦ በዕርዳታ 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ከአውሮፓ ሕብረት በዕርዳታ የብር 230 ሚሊዮን በድምሩ የብር 11 ነጥብ 8 ቢሊዮን የተጨማሪ የበጀት ድጋፍ ስምምነቶች መደረጋቸውን አብራርተዋል፡፡

በአጠቃላይ ከቀጥታ ድጋፍ እና ከሀገር ውስጥ ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች 12.5 ቢሊዮን ብር እንደሚገኝ ታሳቢ ተደርጎ በጀቱ መቅረቡ የተነገረበት የምክር ቤቱ ስብሰባ፣ በሀገር ውስጥ ባንክ ብደር የሚሸፈን 26 ቢሊዮን ብር የፌዴራል መንግሥት ተጨማሪ በጀት እና የወጪ አሸፋፈን ረቂቅ አዋጁን አዋጅ ቁጥር 1247/2013 አድርጎ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል፡፡

LEAVE A REPLY