ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– አንጋፋው አርቲስት ችሮታው ከልካይ፣ ካሳሁን ፍሰሀ (ማንዴላ)፣ ብሩክታዊት ሽመልስ እና ሌሎችም የተሳተፉበትና ዓባይ ወንዝ ላይ ትኩረቱን ያደረገ “ሂድ ና” የተሰኘ ፊልም ተሠርቶ በቅርቡ ለእይታ እንደሚበቃ የኢፌዴሪ በባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ገልጿል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በሰጠው መግለጫ “በሀገር አቀፍ ደረጃ ከዚህ በፊት ዓባይ ላይ ትኩረት ያደረጉ ፊልሞች ቢሠሩም በቂ ናቸው አይባልም። ‘ሂድ ና’ የተሰኘው ፊልም ግን የዓባይን ወቅታዊ ጉዳይ የሚያሳይ ነው” ያለ ሲሆን፣ ኪነጥበብ በዓባይ ጉዳይ ላይ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሶ “ሂድ ና” የተሰኘው ፊልም የዓባይ ወንዝ መነሻን ጨምሮ አሁናዊ የወንዙን ጉዳይ በአግባቡ የሚያስቃኝ እንደሆነና በሌሎች ዓለማት ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችም ፊልሙን እንዲረዱት በእንግሊዘኛ እና በአረብኛ የጽሑፍ ትርጓሜ (ሰብ ታይትል) እንዲኖረው መደረጉን አመልክቷል።
ፊልሙ የዓባይን ጥቅም ላይ መዋል የሚያመላክት፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚሰጠውን የወደፊት ጥቅም ማሳየት የሚችል መሆኑንና የተፋሰሱ ሀገራትም የኢትዮጵያን እና የዓባይን ጉዳይ እንዲረዱት እንደሚያስችልም ያመለከተው ሚኒስቴሩ፣ ለፊልሙ መሳካት ከፊልሙ አዘጋጆች ጋር በጋራ መሥራቱንም አስታወቋል።
የፊልሙ ጸሐፊ የምሥራች ታደለ፣ የፊልሙ ፕሮዲውሰር እና ዳይሬክተር ቢኒያም ሽፋ ሲሆኑ፣ 1 ሰአት ከ40 ደቂቃ ርዝማኔ ያለው ፊልሙ ሰኔ 6/2013 ዓ.ም በደማቅ ስነ ስርዓት እንደሚመረቅም ተገልጿል።