ጌታቸውን ፈዞና ናወዞ ሳይሆን አትሮንስ ስር ብራና ሲያገላብጥ እንዳገኘኸው ተናገር፡፡
—
በ1756 ዓ.ም. የጎንደር ካይላ ሜዳ ጉባኤ በነበረው የነገረ ክርስቶስ ላይ የነበሩትን ዐረብኛና ግእዝ ምንጮች እያመሳከረ ለኅትመት ሊያበቃ በዝግጅት ላይ ሳለ ማግኘትህን ተናገር፡፡
—
በ89 ዓመቱ 700 ገጽ የሚወጣው መጽሐፍ ጽፎና አሳትሞ ለዳግም ኅትመትና አርትዖት ሲላጋ ሲንከላወስ የነበረ ብርቱ መምህር እንጂ መንፈሱ የዛለ ድኩም አረጋዊ አለማግኘትህን ተናገር፡፡
—
በቅርብ ወራት የነግሕ ጸሎቱ ‹‹ይእዜ ትስእሮ ለገብርከ – ባሪያህን አሰናብተው›› ማለቱ በጥቂት ሕማም ‹አንሱኝ ጣሉኝ› ማለቱን ኩሩ መንፈሱ ተጸይፎ እንጂ የሚሠራውን አጥቶ አረጋውያን መዋያ ውሰዱኝ የሚል ቦዝ ሽማግሌ አለማግኝትህን ተናገር፡፡
—
60 ዓመት ከሞላው ወዲህ ወደ አማርኛ ኅትመት መጥቶ እስከ 90 ዓመቱ በተከታታይ 8 መጻሕፍትን በሚደንቅና በአምሳያ አልባ አርትዖት የጻፈ አረጋዊ እንጂ ጭራ ይዞ ከልጅ ልጆቹ ጋራ ለመጫወት ሰፊ ጊዜ የነበረው አባት አለማግኘትህን ተናገር፡፡
—
ስለሚወዳት አገሩና ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልዕልና ሲል የደም ዋጋ ከፍሎ ተተኩሶበት አጥንቱ እስኪፈለጥ በወታደር ጥይት ተመትቶ በተገፍኦ ቢወጣም ለእናት አገሩ ያለው ፍቅር እስከ መጨረሻዋ ህቅታ ድረስ አለመጓደሉን፣ ስሟ በተነሣ ቁጥር ከርቀት ሆኖ እንደ ነቢዩ ዕዝራ በዐይነ ሕሊና እያያት እየተሳለማት እያለቀሳለት ሳለ፣ ዕንባው ሳይቆም ማግኘትህን ተናገር
—
ተናገር! በአረጋዊነቱ የመጨረሻ ሰዓታት ከመጽሐፉ ኅትመት ያገኘውን ገንዘብ በስውር ለነዳያን ሲያከፋፍል እንዳገኘኸው ተናገር! ክርስትናውን ትሩፋቱን አትደብቅ! ለራሱ ጋሪ ላይ ሆኖ ደክሞ ከሕማሙ ታግሎ ያገኘውን ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ መልሶ በስውር ለነዳያን መመጽወቱን፣ እየሞተ ማኖሩን አትሰውር!
—
እንደ ደሴተ ፍጥሞው ቅዱስ ዮሐንስ፣ እንደ ጋ(ን)ግራ ደሴቱ ዲዮስቆርዮስ በተገፍኦ በሄደበት አንገቱን ደፍቶ ከሰው መንጋ ተከልሎ በተባሕትዎ ከመጻሕፍት ሲነጋገር እንዳገኘኸው ተናገር፡፡
—
መሰቀቁን ተናገር! ያ የአፍርንጅ ሊቃውንት ወረፋ ይዘው የሚያገኙት ሊቅ በአገራዊ ቋንቋ በጻፈ ቁጥር ‹ሊቃውንቱ ምኑ ይሉ፣ የዚያ ብሔር የዚህ ሃይማኖት ምን ሊቀጽሉልኝ ይሆን› እያለ መስጋት መሰቀቁን ተናገር! በየጊዜው በገዛ ወገኖቹ በሚነዛ አሉባልታ፣ ከዐውድ በወጣ የጽሑፉ ትርጓሜ ያለአጽናኝ መተከዙን፣ ትካዜውን ለማባረር አትሮንስ ስር መደፋቱን አትደብቅ!
—
ትሕትናውን አትደብቅ! በቅጽል በውዳሴ ስንጠራው ተሰቅቆ መሸሹን ተናገር! የቈጣጠርንለትን ቅኔ ለከንቱ ውዳሴ ሳይሆን ከልባችን ፍቅሩ አገብሮን መሆኑን ለመግለጽ ለማሳመን አቅቶን በእመቤታችን ስም እስከ መማል ደርሰን ‹‹የእርሷን ስም ከጠራችሁብኝማ የት እደርሳለሁ!›› የሚል ሽጉብ በራሱ ላይ የሰሰተ ምስኪን ሊቅ መሆኑን መስክር!
—
ሁቦ ሉዶልፍ አባ ጎርጎርዮስን ቃለ መጠይቅ አድርጎ በሠራው ሥራ በስሙ የጥናት ማዕከል በቆመባት ምድር አቀርቅሮ ምዕራባዊው የኢትዮጵያ ሥዕለ ሕሊና ላይ የማይቀለበስ መፈንቅል ያደረገው ሊቅ በስሙ የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይብረሪ ሊሰየምለት መሆኑ በመስማቱ ብቻ በሕይወት ያቆየውን አምላክ ሲያመሰገን መታየቱን፣ ብሔራዊ ተገፍዖውን መስክር!
—
መልአከ ሞት ሆይ፡- መንበረ ጸባዖት ይዘኸው ስትቀርብ ፈጣሪያችንን እንዲህ በልልን፡- ዛሬ አንድ ግለሰብ፣ ምሁር፣ ሊቅ ፣ አስተማሪ፣ አጥኚ.፣ መልካም ባልና የልጆች አባት፣ የሴማውያን ልሳናት ተጠሪ፣ የቲዎሎጂ ምሩቅ፣ የሊቀ ሊቃውንት መሓሪ ትርፌ (ኋላ አቡነ ጴጥሮስ) የሐዲሳት ትርጓሜ ደቀ መዝሙር ሳይሆን ግዙፍ ሕያው ተቋም ከነአዕማዱ ይዤ መጣሁ በል! ተናገር!
—
ለእኛም ንገርልን! በዓለም ሥጋ ሳለ በዘወትር ጸሎት ‹‹..ለሣህለ ማርያም ይዕቀቦ…›› እያልን የምንጠራውን አባት በዓለመ ነፍስ አስቦ ‹‹…ለነፍሰ ሣህለ ማርያም ያድኅና…›› ብሎ ንባብ ቀይሮ ለመጸለይ አንደበታችን መያያዙን፣ ዳዊታችን በዕንባ መርጠቡን፣ የዕጓለ ማውታ ስሜት ውስጥ መሆናችንን፣ መዋዕለ ፍጻሜውን በሙሽራ መንፈስ ለማድረግ ስንመኝ ተነጥቀን የመዘረፍ ስሜት ውስጥ መግባታችንን፣ ደግሶ ሙሽራው የቀረበት ባለወግ ማዕረግ የሚሰማው ስሜት ውስጥ መግባታችንን ንገርልን! በእርሱ መጠራት ድኩማን የመንፈስ ልጆቹ የጎደልንን የጎደለብን ንገርልን!