ዶ/ር ዐቢይ አሕመድና አቶ ደመቀ መኮንን ወቅታዊ መልዕክት አስተላለፉ!

ዶ/ር ዐቢይ አሕመድና አቶ ደመቀ መኮንን ወቅታዊ መልዕክት አስተላለፉ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ ዛሬ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የክብ ባህላችን” በሚል በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት “ቤታችን፣ ምጣዳችን፣ ድስታችን፣ ሌማት ገበታችን፣ እንጀራ ዳቧችን፣ስኒ ጀበናችን ሁሉ ክብ ነው። በክብ እንኖራለን፤ ከብበን እንበላለን። ከብበን እንዘፍናለን፤ ከብበን እናለቅሳለን። በክብ ውስጥ ሁሉም እኩል መቀመጫ እኩል ድርሻ አለው። ክብ የሙሉነት፣ የፍጽምና፣ የወሰን የለሽነት፣ የዘላለማዊነትና የእኩልነት ተምሳሌት ነው። እንጀራ ቆራርጠን ለየብቻ መብላት ከመጀመራችን በፊት በትልቁ ባላአንበሳ ትሪ ወይንም ሌማት ላይ ተዘርግቶ፣ ወጡ ከመሐል ላይ ወጥቶ፣ ሁሉም በጋራ ይቋደስ ነበር። በክብ ጥቅልል ጉርሻ ፍቅራችንን መጋራት የተለመደ ነው። ከእንስራና ጋኑ እየተቀዳ ጠላና ብርዙ ሁሉም ከቀንድና ከቅል በተሠሩ ክብ መጠጫዎች በጋራ ይጎነጭ ነበር። ዛሬም ኢትዮጵያን እንክበብ። አንድነትና ሙሉነታችንን፣ መያያዝ መፋቀራችንን ሊከፋፍሉና ሊሸራርፉ የሚገዳደሩንን እንድናሸንፍ ማንንም ጣልቃ የማያስገባ ክብ እንፍጠር። በእኩልነትና በመያያዝ አንድነታችንንና ፍጹም ሙሉነታችንን ለዓለም ሕዝብ እናሳይ” ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ባስተላለፉት የተንቀሳቃሽ ምስል መልእክታቸው “በሰብዓዊነት ሽፋን የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት፣ ሉዓላዊነት፣ አብሮነት እና የመንግሥትን ተግባር የሚያቃልል ተልዕኮ ተቀባይነት የለውም፡፡

በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታን ከፍ ለማድረግ፣ የመልሶ ግንባታ እና መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለመጀመር ኢትዮጵያ ከኹሉም ባለድርሻ እና ይመለከተኛል ከሚል አካል ጋር ለመሥራት ዝግጁ ናት። በዚህ ወቅት ጫና ሳይሆን ድጋፍ ነው የሚያስፈለጋት። በትግራይ ክልል ያለውን ችግር ማሻሻል የሚቻለው የሰብዓዊ እርዳታን ተደራሽነት በማፋጠን ከመንግሥት ጋር በመሥራት ነው። …

የኢትዮጵያ መንግሥት ለዜጎቹ የሚጠበቅበትን ኀላፊነት እና በዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕጎች መሠረት መወጣት ያለበትን ግዴታዎች በሚገባ ያውቃል” በማለት ይህንን ኃላፊነቱን ለመወጣት ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ መሆኑን እና በጎ ፍቃደኞች ሁሉ ጥረቱን በመደገፍ ከጎኑ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

LEAVE A REPLY