የባልደራስ አመራሮች ጥያቄ በፍ/ቤት ውድቅ ሆነ! እስክንድር ከቂሊንጦ መልዕክት አስተላለፈ!

የባልደራስ አመራሮች ጥያቄ በፍ/ቤት ውድቅ ሆነ! እስክንድር ከቂሊንጦ መልዕክት አስተላለፈ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ባልደራስ ፓርቲ፣ ሰኔ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ፍ/ብሔር ችሎት “እነ እስክንድር ነጋ ያለመከሰስ መብታቸው ተጠብቆ ከእስር እንዲለቀቁ” ሲል ላቀረበው አቤቱታ ፍ/ቤቱ ዛሬ ብይን ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ በዛሬው ውሎ፣ እነእስክንድር በ6ኛው አገራዊ ምርጫ እጩ ሆነው መቅረባቸውን አረጋግጦ፣ ከእስር እንዲፈቱ በጠበቆች ለቀረበው አቤቱታ በሰጠው ምላሽ “የወንጀል ክሱ የተመሠረተው እጩ ሆነው ከመመዝገባቸው በፊት ስለሆነ ጥያቄውን አልተቀበልኩትም” በማለት በእስር ላይ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ብይን ሰጥቷል።

ብይኑን ተከትሎ የፓርቲው የህግና የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ኃላፊ ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ በሰጡት መግለጫ “በብይኑ ላይ ቅሬታ ስላደረብን ይግባኝ ለጠቅላይ ፍ/ቤት በማዘጋጀት ላይ እንገኛለን” ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የአንጋፋውን የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ሊቅ፣ የፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌን ሕልፈተ ሕይወት በተመለከተ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዚዳንቱ እስክንድር ነጋ ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ባስተላለፈው የሐዘን መልዕክት “መካሪዬ፣ አባቴ፣ አስተማሪዬ የሆኑት በማረፋቸው በጣም አዝኛለሁ። ጓጉተውለት የነበረውን የዘንድሮ ምርጫ ውጤት አይተው ቢሆን ኖሮ ጥሩ ነበር፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ፈቃዱ አልሆነም። የሰላም እረፍት ይሁንላቸው። ለቤተሰቦቻቸው፣ ዘመዶቻቸው እና ጓደኞቻቸው መፅናናትን እመኛለሁ” ብሏል።

LEAVE A REPLY