ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነገ በሚያካሂደው 6ኛ ዓመት 15ኛ መደበኛ ስብሰባው በመጪው 2014 ዓመት ረቂቅ በጀት ላይ እንደሚወያይ ተገልጿል።
በነገው የምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ ተገኝተው የፌደራል መንግሥት ለ2014 በጀት ዓመት ባዘጋጀው ረቂቅ በጀት ላይ መግለጫ እንደሚያቀርቡ የተነገረ ሲሆን፣ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በመወያየት የተለያዩ የውሳኔ ሐሳቦችን እንደሚያጸድቅና በሚቀርብለት የበጀት መግለጫ ላይ ተወያይቶ ረቂቅ የበጀት አዋጁን ለዝርዝር እይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ እንደሚመራ ይጠበቃል።
በተጨማሪም የመንግሥት ወጪ፣ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የውጭ ኦዲት ድግግሞሽን ለማስቀረት የወጣ የነጠላ ኦዲት ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ እንደሚያጸድቅ የሚጠበቀው የነገው የምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ የሂሳብ ምርመራ ኮርፖሬሽንን እንደገና ለማቋቋም የወጣ ረቂቅ ደንብን አስመልክቶ ከቋሚ ኮሚቴው የሚቀርብለትን ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ ተወያይቶ ያጸድቃልም ተብሏል።