ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– “የኮሮና ቫይረስ ታካሚዎችን በሚሊየን ብር ያስከፍላል ተብሎ በኢሳት ቴሌቭዥን የቀረበብኝ ዜና ሐሰተኛ ከመሆኑም ባሻገር በጎ ስሜን ለማጥፋት የቀረበ ነው” ሲል ሃሌሉያ አጠቃላይ ሆስፒታል ቅሬታውን ገልጾ፣ ጉዳዩንም ወደ ፍርድ ቤት እንደወሰደው አስታውቋል።
የሆስፒታሉ አስተዳደሮች ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ሆስፒታሉ ከ735 በላይ ለሚሆኑ የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎች በተመጠጣኝ ዋጋ የህክምና ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰው “አንድ በርከት ያለ ተጓዳኝ በሽታ ያለባቸውና በፅኑ ህሙማን ክፍል በማሽን እየታገዙ ሲተነፍሱ የነበሩ ሕይወታቸው ያለፈ ታካሚ ያወጡትን ወጪ ብቻ አይቶ ሃሌ ሉያ ሆስፒታል የኮሮና ቫይረስ ታካሚዎችን በሚሊዮን ብር ያስከፍላል ተብሎ በኢሳት ቴሌቭዥን የቀረበው ዜና ሐሰተኛ እና በጎ ስማችንን ለማጥፋት የቀረበ ነው” ብለዋል።
“ዜናው ስለእኛ ሆኖ ሳለ እኛ ሳንጠየቅ አንዴት ይተላለፋል?” ሲሉ የጠየቁት የሆስፒታሉ ባለቤት ፕሮፌሰር ጌታቸው አደራዬ “ዜናው ሚዛናዊነት ይጎለዋል እንዳይተላለፍ ብለን በፍርድ ቤት ብናሳግድም ኢሳት ህጉን ጥሶ አስተላልፏል። በዚህም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደነዋል” በማለት ጉዳዩን አስመልክተው ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።