– 45 ሺ የምርጫ ታዛቢዎች ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ምርጫ ቦርድ ገለጸ!
ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– 6ኛው አገራዊ ምርጫ በሚካሄድበት የፊታችን ሰኞ ሰኔ 14 ቀን ሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዝግ እንደሚሆኑ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዛሬ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰራጩት መልዕክት አስታውቀዋል።
ጠ/ሚኒስትሩ በዚሁ መልዕክታቸው “ሰኔ 14፣ 2013 ሁለት ነገር እንትከል። በካርዳችን ዴሞክራሲን፣ በእጃችን ችግኞችን። ድምጻችንን ለመስጠት ሰኔ 14 ቀን በነቂስ እንውጣ። አረንጓዴ ዐሻራችንን በማሳረፍ፤ ኢትዮጵያን ለማልበስ የሚደረገውን ጥረት እንቀላቀል። ሁሉም የመንግስት መስሪያ ቤቶች በዕለቱ ዝግ ይሆናሉ። እሱንም ለማካካስ ቀጥሎ በሚመጣው ቅዳሜ ወደ ስራ የምንገባ ይሆናል” ብለዋል።
በተመሳሳይ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት “የዛሬ ሳምንት ኢትዮጵያውያን በ6ኛው ብሔራዊ ምርጫ ድምፃችንን እንሰጣለን። ይህ ምርጫ በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሚሆን ነጻ እና ፍትሐዊ ምርጫ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን። መላው ኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ መብቶቻችንን ለማስከበር ወደ ምርጫው በምንሄድበት ወቅት ቀኑን የዜግነት ግዴታችንን በመወጣት የትውልድ ማኅተም ለመተው እንድንጠቀምበት እጠይቃለሁ፡፡ በመጪው ሰኞ ውጡና ድምጽ ስጡ፡፡ አረንጓዴ ዐሻራችሁንም አስቀምጡ፡፡ ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነን ቀኑን ታሪካዊ የዴሞክራሲ ቀን እናድርገው!” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በሌላ በኩል፣ ሰኔ 14 ለሚካሄደው ምርጫ የሚያገለግሉ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ከትናንት አመሻሽ ጀምሮ ወደ ምርጫ ክልሎች መሰራጨት እንደጀመሩ አዲስ ዘይቤ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማረጋገጥ ችላለች።
የድምጽ አሰጣጡ የሚካሄደው በ44,372 የምርጫ ጣቢያዎች እንደሆነ ትናንት በሰጡት መግለጫ የገለፁት የምርጫ ቦርድ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሶሊያና ሽመልስ “ቦርዱ እስካሁን ሲያጓጉዝ የቆየው ለምርጫ አስፈጻሚዎች ስልጠና የሚውሉ ሰነዶችን እንዲሁም ከፍተኛ ጥንቃቄ የማይጠይቁ እንደ ማሸጊያ ሳጥን አይነቶቹን ቁሳቁሶችን ሲሆን፣ የድምጽ መስጫ ወረቀቶችን ወደ ምርጫ ክልሎች ማጓጓዙ ዛሬ ምሽት ይጀምራል። የድምጽ መስጫ ወረቀት ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ (sensitive material) ስለሆነ ቀኑ (ለምርጫ) በተጠጋ ቁጥር ማድረስ ስላለብን ነበር እስካሁን የዘገየነው” ሲሉ አስረድተዋል።
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊዋ ከዚሁ ጋር በማያያዝም፣ በ6ተኛው ሀገራዊ ምርጫ ከሲቪክ ማህበራት የተውጣጡ 45 ሺ የሀገር ውስጥ የምርጫ ታዛቢዎች እንደሚሳተፉ አስታውቀው፣ ምርጫውን ለመታዘብ ከ102 የሲቪክ ማህበራት የተወከሉ 45 ሺ የሀገር ውስጥ የምርጫ ታዛቢዎች ለመታዘብ የሚያስችላቸውን ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን አመልክተዋል።
ከሀገር ውስጥ የምርጫ ታዛቢዎች በተጨማሪ እስካሁን ቁጥራቸው በትክክል ያልታወቀ የውጭ ሀገር ታዛቢዎች ምርጫውን ለመታዘብ ቅድመ ሁኔታዎችን እያጠናቀቁ መሆናቸውን የጠቆሙት ሶሊያና ሽመልስ፣ ከምርጫው ቀን አስቀድሞ በግልፅ ቁጥራቸው የሚቀመጥ መሆኑንም ገልጸዋል።