የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2014 በጀት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል አሳሰበ!

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2014 በጀት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል አሳሰበ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ዛሬ ባካሄደው 15ኛ መደበኛ ስብሰባ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ለ2014 በጀት አመት ያቀረቡትን ዝርዝር የበጀት መግለጫ ካዳመጠ በኋላ፣ የተመደበው በጀት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል በፕሮግራም በጀት አጠቃቀም ላይ ልዩ ክትትል መደረግ እንዳለበት አሳስቧል፡፡

በ2014 በጀት ዓመት አጠቃላይ የበጀት ዝርዝር መግለጫ ላይ የተወያየው ምክር ቤቱ፣ በቀረበው የበጀት መግለጫ ላይ በጥልቀት ከተወያየ በኋላ ረቂቅ የበጀት አዋጁን ለዝርዝር እይታ ለገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የላከው ሲሆን፣
የምክር ቤቱ አባላትም የተመደበውን በጀት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋልና ኢኮኖሚውን ለማሳደግ መንግሥት በአገሪቱ እየተከሰተ ያለውን የዋጋ ንረት መቆጣጣር እንዳለበት አስታውሰው፣ ይህን ማድረግ ካልተቻለ የዋጋ ንረቱ ወደ ነጠላ አኃዝ ከመውረድ ይልቅ ሊጨምር እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልፀዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴም ለ2014 በጀት አመት ብር 561.7 ቢሊዮን አጠቃላይ ወጪ በጀት መመደቡን፣ ከዚህ ውስጥ ለመደበኛ ወጪ ብር 162.2፣ ለካፒታል ወጪ መሸፈኛ ብር 183.5 ቢሊዮን፣ ለክልል መንግሥታት የበጀት ድጋፍ ብር 204 ቢሊዮን እና ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈፀሚያ ብር 12 ቢሊዮን ተደግፎ እንደቀረበ አስረድተው፣ የፕሮግራም በጀት አጠቃቀምን ለማጠናከር በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩል ክትትል እንደሚደረግና የግብርና ምርቶችን በማሳደግና የንግድ ሥርዓቱን በማዘመን በአገሪቱ እየተከሰተ ያለውን የዋጋ ንረት ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን ነው ለምክር ቤት አባላት አብራርተዋል።

አያይዘውም፣ ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የተመደበላቸውን በጀት ለታለመለት ዓላማ በቁጠባና በውጤታማነት ጥቅም ላይ ማዋል እንዳለባቸው ማሳሰባቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

LEAVE A REPLY