ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ኳታር ላይ በተጠራው ስብሰባ የአረብ ሊግ በህዳሴ ግድብ ላይ ያሳለፈው ውሳኔ ሚዛናዊነት የጎደለው እና ኢፍትሐዊ መሆኑን የኢትዮጰያ መንግሥት አስታውቆ ውሳኔንም “የአባይን ወንዝ በትብብር እና በዘላቂነት ለመጠቀም የማያስችልና ዓለም አቀፍ ሕጎችን የሚጻረር ነው” ብሎታል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ፣ ውሳኔው የአረብ ሊግ አባል ሀገራት የአባይ ወንዝን አጠቃቀም እና የኢትዮጵያን የነበረ አቋም ካለማወቅ የመጣ መሆኑን ገልጾ “የሕዳሴው ግድብ በሚሊየን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን ከድህነት የሚያወጣ፣ የኃይል አቅርቦት እና የምግብ ዋስትና የሚረጋገጥበት ፕሮጀክት መሆኑን ሁሉም በውል ሊገነበዘበው ይገባል” ብሏል፡፡
በመግለጫ አያይዞም፣ አባይ የጋራ ሀብት እንጂ የተናጠል የግብጽ እና የሱዳን ሀብት አለመሆኑን፤ ይሁን እንጂ የተፋሰሱ ሀገራት በትብብር እና በውይይት የውኃ ደህንነት ማረጋገጫ መንገድ እንደሆነ የኢትዮጵያ ጽኑ እምነት መሆኑን አመልክቶ፣ ኢትዮጵያ የሁለቱን ሀገራት ስጋት ግምት ውስጥ ያስገባ፣ የታችኞቹን የተፋሰስ ሀገራት በጋራና በትብብር መንፈስ እንጠቀም መርህን አሁንም አጠናክራ እንደምትቀጥል በማስታወቅ “በህዳሴው ግድብ ጉዳይ ላይ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር የሚደረገውን ድርድር የአረብ ሊግ አባል ሀገራት በሚገባ ሳያጤኑ ያደረጉትን ሚዛናዊነት የጎደለው ውሳኔ በድጋሚ እንዲመለከቱት” ሲልም አሳስቧል።
የአረብ ሊግ ስብሰባ እና የኢትዮጵያ ምላሽ የዐረብ ሊግ የተመድ ጸጥታው ም/ቤት ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ባለችው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ስንብሰባ እንዲያደርግ ትላንት ባደረገው ስበባ ጠይቋል።የሊጉ አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባደረጉት ሰብሰባ የሁሉንም አካላት ፍላጎት የሚያሳካ አስገዳጅ ስምምነት ላይ መደረስ እንዳለበት አንስተዋል።
የዐረብ ሊግ አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በኳታር መዲና ዶኃ ባደረጉት ስብሰባ፣ በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት እየተካሄደ ያለውን ድርድር “አዝጋሚ ነው” ሲሉ ገልጸው፣ በመሆኑም የጸጥታው ም/ቤት በግድቡ ዙሪያ ስብሰባ እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረባቸውን ዘገባዎች አመልክተዋል።