ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በዘንድሮው ምርጫ በአዲስ አበባ ጠንከር ፉክክር ሊኖር እንደሚችል የፖለቲካ ፓርቲዎችን ቁጥር መጨመርና ስመ ጥር ፖለቲከኞች በዕጩነት መቅረባቸው ማሳያ መሆኑ እየተነገረ ነው።
ለመሆኑ በአዲስ አበባ ለከተማዋ ምክር ቤት እና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፍተኛ ፉክክር ያደርጋሉ የሚባሉት ብልጽግና ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ሲሆኑ ያቀረቧቸው እጬዎችም ታዋቂና ሰፊ የፖለቲካ ልምድ ያላቸው እንደሆኑ ይነገራል።
በዚህም መሰረት፣ ጠንካራ ፉክክር ከሚጠበቅባቸው የአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች አንዱ በሆነው ቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፓርቲ በቂርቆስ ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የምጣኔ ሃብት ባለሙያውንና የቀድሞ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የነበሩትን አቶ ክቡር ገናን በዕጩነት ያቀረበ ሲሆን፣ ብልጽግና በበኩሉ የመከላከያ ሚንስትሩን ቀነኣ ያደታ (ዶ/ር)፣ የትምህርት ሚኒስትሩን ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጀነር) እና የቀድሞ የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪ የአሁኑ የሥራ ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሸነር አቶ ንጉሡ ጥላሁንን ለከተማው ምክር ቤት በዕጩነት አቅርቧል።
በንፋስ ስልክ ብልጽግና የመዲናዋን ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤን፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ደግሞ በእስር ላይ ያሉት አቶ ስንታየሁ ቸኮልን በንፋስ ስልክ ላፍቶ የምክትል ከንቲባዋ ተፎካካሪ አድርጎ አቅርቧል።
በቦሌ ብልጽግና ፓርቲ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ የሆኑትን አቶ ዣንጥራር አባይን ለአዲስ አበባ ምክር ቤት፣ እንዲሁም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒሰትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በምርጫ ክልል 3 የጤና ሚንስትሯን ዶ/ር ሊያ ታደሰን፣ በእጩነት ሲያቀርብ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ ዶ/ር ጥላሁን ገብረ ሕይወትን በዚሁ ምርጫ ክልል ያወዳድራል። በምርጫ ክልል 6 የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲን በመወከል አቶ ግርማ ሰይፋ የሚወዳደሩ ሲሆን ብልፅግና ፓርቲ ደግሞ በምርጫ ክልል 6 ዶ/ር ኢ/ር ወንድሙ ተክሌን አቅርቧል።
ብልጽግና በምርጫ ክልል 7 በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የኢትዮጵያ አቋም ለአረቡ ዓለም በማንጸባረቅ የሚታወቁት መሐመድ ከማል አሊ አል-አሩሲ ዕጩ ሆነው የቀረቡ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ ደግሞ ናርዶስ ስለሺን ተወዳዳሪ አድርጓል። የትራንስፖርት ሚንስትሯ ዳግማዊት ሞገስ ደግሞ ብልጽግናን በመወከል በምርጫ ክልል 8 በዕጩነት ቀርበዋል።
በምርጫ ክልል 11 ፕ/ር ሂሩት ወ/ማርያም ብልጽግናና በመወከል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ሲሆኑ፣ ሰለሞን ተሰማ (ዶ/ር) ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ እንዲሁም የጁአልጋው ጀመረ ደግሞ ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ ቀርበዋል።
የኢዜማ ምክትል መሪ አንዱዓለም አራጌ የምርጫ ክልል 12 እና 13 ዕጩ ሲሆኑ ዶ/ር ስንታየሁ ወ/ሚካኤል ደግሞ ብልጽግና ፓርቲን በመወከል ቀርበዋል። የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚንስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር፣ ኢንጂነር) በአዲስ አበባ ምርጫ ክልል 17 የብልጽግና ፓርቲን በመወከል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነት ዕጩ ሆነዋል። ከስለሺ በቀለ (ዶ/ር፣ ኢንጂነር) ጋር ተፎካካሪ ሆነው ከቀረቡት መካከል የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በቃሉ አጥናፉ ተጠቃሽ ናቸው።
በምርጫ ክልል 18 ዛዲግ አብርሀ የብልጽግና ፓርቲ ዕጩ ሆነው የቀረቡ ሲሆን በምርጫ ክልል 20 የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከብልጽግና ፓርቲ ዕጩ ሆነዋል። ከአምባሳደር ዲና ጋር ተፎካካሪ ሆነው ከቀረቡት መካከል የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የጽሕፈት ቤት ኃላፊው ገለታው ዘለቀ ይገኙበታል።
በምርጫ ክልል 21 እና 22 የብሔራዊ ባንክ ገዢው ዶ/ር ይነገር ደሴ የብልፅግና ፓርቲን ሲወክሉ፤ በተመሳሳይ የምርጫ ክልል የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓቲው ኢ/ር አንተነህ በለው እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ አባይ ብርሀኑ ወ/ጊዮርጊስ ዕጩ ናቸው።
በምርጫ ክልል 23 ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲን ወክለው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወዳዳሪ ሲሆኑ፣ የብልጽግናው የአገር አቀፍ ምዘና እና ፈተናዎች ኤጀንሲ ዳይሬክተር ዲላሞ ኦቶሬ ደግሞ ብልጽግናን በመወከል ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጋር ይፎካከራሉ።
ብልጽግና ፓርቲ ወኪሉን ባላቀረበበት ምርጫ ክልል 28፤ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በግል ተወዳዳሪነት ቀርበዋል። አማሃ ዳኘው ደግሞ በምርጫ ክልል 28 ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲን ወክለው ይወዳደራሉ። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ በበኩሉ በዛብህ ደምሴ (ዶ/ር) አቅርቧል።
በየካ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ በእስር ላይ ያሉትንና የፓርቲውን ፕሬዚዳንት አቶ እስክንድር ነጋን ለከተማዋ ምክር ቤት ወንበር አቅርቧል።
አራዳ በአራዳ ከፍለ ከተማ የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ዳባ ደበሌ የብልጽግና ፓርቲን ወክለው በዕጩነት ቀርበዋል። ከአቶ ዳባ በተጨማሪ አቶ ነብዩ ባዬ ብልጽግና ፓርቲን ወክለው ዕጩ ሆነው ቀርበዋል።
በኮልፌ ቀራኒዮ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ ብልጽግናን ወክለው ቀርበዋል። ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በበኩሉ የህግ ባለሙያው ሄኖክ አክሊሉን የኮልፌ ቀራኒዮ ዕጩ አድርጎ አቅርቧል።
የአውሮፓ ህብረት የዛሬ መግለጫ፤
ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የአውሮፓ ህብረት ዛሬ ባወጣው መግለጫ ለምርጫ 2013 የታዛቢ ቡድን መላክ ባለመቻሉ መጸጸቱን አስታውቋል፡፡
ከወር በፊት ህብረቱ ለመታዘብ ያስችሉኛል ባላቸው ሁኔታዎች ዙሪያ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ባደረገው ውይይት አለመስማማቱን ገልጾ፣ የመታዘብ እቅዱን ማንሳቱን አስታውቆ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የአውሮፓ ህብረት ምርጫውን ለታዘብ ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ሉዓላዊነትን ስለሚጋፉ ስለሆኑ ህብረቱ ምርጫ ለመታዘብ ያስቀመጣቸውን ቅድመ ሁኔታ እንደማይቀበል ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስት አቋሙን ካሳወቀ በኋላ ህብረቱ የምርጫው እለት ልኡክ እንደሚልክ አስታውቆ ነበር፡፡
ህብረቱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ግን በድጋሚ ምርጫውን የሚታዘብ ልዑክ መላክ እንደማይችል እና በድርጊቱ ማዘኑን ገልጾ፣ ከነገ በስቲያ ማለትም ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም የሚካሄደው ምርጫ ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ለውጥ ሂደት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውና ህብረቱ በቀጣይ ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አብሮ እንደሚሰራ አስታውቋል።